ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እስራኤል ታሪካዊ የተባለውን የአሜሪካ እና የአረብ ሃገራት ስብሰባ እያስተናገደች ነው
አራት የአረብ ሊግ አባል አገራት እና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በእስራኤል ታሪካዊ የተባለለት ስብሰባ እያደረጉ ነው።
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች፣ የሞሮኮ እና የባህሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከእስራኤሉ አቻቸው ጋር በእስራኤል ሲገናኙ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ይህ ሊሆን የቻለው ባለፉት 18 ወራት የአረብ አገራቱ ከእስራኤል ጋር ያላቸውን ግንኙነት ካሻሻሉ በኋላ ነው።
የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም የስበሰባው ተሳታፊ ናቸወ።
እአአ በ1979 ከእስራኤል ጋር ሠላም ያወረደች የመጀመሪያዋ የአረብ ሀገር ግብፅ ነበረች። የሁለቱ አገራት ግንኙነቱ ግን አንዴ ሞቅ ሌላ ጊዜ ደግሞ ሲቀዛቀዝ ቆይቷል።
ስድስቱ ከፍተኛ ዲፕሎማቶች በደቡባዊ እስራኤል ኔጌቭ በረሃ ውስጥ በሴዴ ቦከር በሚባል ስፍራ በሚገኝ ሆቴል ተገናኝተዋል።
ስብሰባው የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በአካባቢው አገራት እያደረጉት ካሉት ጉብኝት ጋር ተገናኝቷል።
ብሊንከን በአምስት ቀናት ቆይታቸው እስራኤልን፣ ዌስት ባንክን፣ ሞሮኮን እና አልጄሪያን ይጎበኛሉ።
ብሊንከን ስለዩክሬን ግጭት፣ ከኢራን ጋር ስላለው ውጥረት እና በእስራኤል-ፍልስጤም ግጭት ዙሪያ የሚመክሩበት ጉዳዮች ናቸው።
ብሊንከን የእስራኤሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔትን በእየሩሳሌም እንዲሁም የፍልስጤሙን ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስን በራማላህ አግኝተው አነጋግረዋል።
ቤኔት ከብሊንከን ጋር ስብሰባውን ያካሄዱት በማዕቀብ የተሽመደመደችው ኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብሯን ለመግታት ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር አዲስ ስምምነት ልትፈራረም ነው የሚል ስጋት በእስራኤል እየጨመረ ባለበት ወቅት ነው።
የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እአአ 2015 ላይ አገራቸው እና ምዕራባውያን ከኢራን ጋር የተደረሰውን የኒውክሌር ስምምነት ጥለው ወጥተዋል።
ይህን ተከትሎ ኢራን በስምምነቱ የተከለከለውን የኒውክሌር እንቅስቃሴዋን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ ችላለች።
አዲስ የሚደረስ ስምምነት የበለጠ ደካማ ይሆናል የምትለው እስራኤል፤ ይህም ኢራን በአካባቢው ያላትን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ለማጠናክር እንደምትሠራ ትናገራለች።
የእስራኤል ሌላው ፍራቻ አዲሱ የኒውክሌር ስምምነት ዩናይትድ ስቴትስ የኢራንን እስላማዊ አብዮት ጠባቂን (አይአርጂሲ) ከአሸባሪ ቡድኖች ዝርዝር ውስጥ ልታስወግድ ትችላለች የሚለው ነው።
አይአርጂሲ በሶሪያ እና በየመን ያለውን ጦርነት ለማስቀጠል እና በጋዛ፣ ሊባኖስና ሶሪያ ያሉ ፀረ እስራኤል ታጣቂ ቡድኖችን በማጠናከር እገዛ አድርጓል ስትል እስራኤል ትከስሳለች።
ብሊንከንም በእስራኤል-ፍልስጤም ጉዳይ ከቤኔት የተለየ ሃሳብ አላቸው። የፍልስጤም ግዛት ከእስራኤል ጎን ለጎን እንዲሆን ቢደግፉም የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ፍርጥም ብለው ውድቅ አድርገውታል።
እስራኤል በግንባር ቀደምትነት የሽምግልና ሚና የምትጫወትበት የሩሲያ እና ዩክሬን ግጭትም የውይይቱ አካል ነው።
እስራኤል ከዩክሬን እና ከሩሲያ ጋር ጥሩ ግንኙነት አላት። ቤኔት በዩክሬን ለአንድ ወር የዘለቀውን ጦርነት ለማስቆም በሚደረገው ጥረት ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ለበርካታ ጊዜ በአካል እና በስልክ ውይይት አድርገዋል።