"ለአምስት ደቂቃ ይህችን ዓለም ተሰናብቼ ነበር" - ክሪስቲያን ኤሪክሰን

ክሪስቲያን ኤሪክሰን
የምስሉ መግለጫ, ክሪስቲያን ኤሪክሰን
ታትሟል

ክሪስቲያን ኤሪክሰን ወደ እግር ኳስ ሕይወት ተመልሶ ከብሬንትፈርድ ጋር መጫወት መቻሉን እንደ ተዓምር እንደሚያየው ይናገራል።

ኤሪክሰን ባለፈው የአውሮፓ ጨዋታ ለሃገሩ ዴንማርክ እየተጫወተ ሜዳ ላይ ተዝለፍልፎ መውደቁ አይዘነጋም።

የ29 ዓመቱ ዴንማርካዊ አይሲዲ የተሰኘ የልብ አጋዥ መሣሪያ ተገጥሞለት ነው ወደ ሜዳ የተመለሰው።

ኤሪክሰን የቀድሞ ክለቡ ኢንተርሚላን ከለቀቀው በኋላ ከብሬንትፈርድ ጋር ለስድስት ወራት የሚያቆየውን ስምምነት ፈርሟል።

ኤሪክሰን ለዚህ ምስጋናዬን አቀርባለሁ ሲል ለቢቢሲ ስፖርት ይናገራል።

"ለኔ ክስተቱ ዕድለ ቢስ ነገር ግን ቦታው ደግሞ ዕድለኛ የሚያስብል ነው። በዙሪያዬ ያሉ ሰዎች በፍጥነት ሁሉን ስላደረጉ ዕድለኛ ነኝ። ዶክተሮች በዙሪያዬ ስላሉም አመሰግናለሁ።"

ኤሪክሰን አሁን በጣም በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝና ወደፊት ደግሞ ከአደጋው በፊት ወደነበረ አቋሙ ለመመለስ እንደሚሠራ አልፎም ምንም የሚያስፈራው ነገር እንደሌለ ይናገራል።

"የጨዋታ ፍሰቴን አልቀይርም" ይላል ኤሪክሰ። "አሁን ጥሩ ስሜት ላይ ነኝ። ወደቀደመው አቋሜ የማልመለስበት ምክንያት አይታየኝም።"

"ለአምስት ደቂቃ ይህችን ዓለም ተሰናብቼ ነበር"

በፈረንጆቹ ሰኔ 12/2021፤ ይህች ቀን ለኤሪክሰን ልዩ ትርጉም አላት። በዚህ ቀን የሆነውን ሁሉን ነገር ያስታውሳል። ከአምስት ደቂቃ በቀር።

አምስቷን ደቂቃ "ከዚህች ዓለም ከተሰናበትኩ በኋላ መልሶ ልቤ እንዲመታ ያደረጉበት ቅፅበት" ሲል ይገልፃታል።

የአውሮፓ ዋንጫ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን እያደርጉ የሚገኙት ዴንማርክና ፊንላንድ ከመጀመሪያው አጋማሽ በፊት ከኳስ ጋር ትግል ላይ ነበሩ።

ድንገት 41ኛው ደቂቃ ላይ ዴንማርካዊው አማካይ ተዝለፍልፎ ሜዳ ላይ ወደቀ። ለ15 ደቂቃ ያክል ሲፒአር ከተሰጠው በኋላ በቃሬዛ ከሜዳ እንዲወጣ ተደረገ።

ኤሪክሰን የነቃው ሆስፒታል ከተወሰደ በኋላ ነበር።

ክሪስቲያን ኤሪክሰን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጨዋታው ከሶስት ሰዓታት በኋላ ድጋሚ ተደርጎ ፊንላንድ 1 ለምንም ፍልሚያውን መርታቱ አይዘነጋም።

"ከአምስት ደቂቃ በቀር ሁሉን ነገር አስታውሳለሁ። ኳስ በእጅ ሲወረወር፤ ጉልበቴን ሲመታኝ፤ ከዚያ በኋላ የሆነውን ጭራሽ አላስታውስም።"

"ከዚያ ስነቃ ሰዎች ከበውኛል። ደረቴን ይጫኑኛል። ትንፋሼን ለመመለስ ይታገላሉ። ከዚያ ተነሳሁ። ዓይኔን ስገልጥ በዙሪያዬ ሰዎች አየሁ። ምን እየሆነ እንደሆነ አልገባኝም ነበር።"

ቀጥሎ አንድ ሰው አምቡላንስ ውስጥ 'ለምን ያክል ጊዜ ነው ትንፋሹ ተቋርጦ የነበረው?' ሲል ሰማሁ። መላሹ ደግሞ 'አምስት ደቂቃ' ይላል። ትንፋሼ ተቋርጦ እንደነበር የገባኝ የዚያኔ ነው።"

'ወደ ሜዳ መመለስህ እንደ ተዓምር ነው የምታየው?' ተብሎ የተጠየቀው ኤሪክሰን "አንዴታ። ወደ ሜዳ ስመለስ ደግሞ የበለጠ እውነታው ይገባኛል። ስታድዬም ውስጥ ስገኝ። ጨዋታ ስጫወት። የሚፈጥረው ስሜት ለየት ያለ ነው።"

"ምንም ነገር ቢፈጠር አንዳች ነገር አልሆንም።"

ክሪስቲያን ኤሪክሰን በአንቶኒዮ ኮንቴ ዘመን የጣልያን ሴሪ ኤ ዋንጫን ከኢንተር ጋር አንስቷል።

ኤሪክሰን ከክለቡ ኢንተር ሚላን ጋር ባለፈው ታኅሣሥ በስምምነት የተለያየው አይሲዲ የተገጠመለት ሰው በሴሪ ኤ መጫወት ስለማይችል ነው።

ነገር ግን የእንግሊዝ ፕረሚዬር ሊግ እንዲህ ዓይነት ሕግ የለውም።

ኤሪክሰን፤ ከኢንተር ሚላን ጋር በስምምነት ከተለያየ በኋላ ሃገሩ ዴንማርክ በሚገኘው ኦዴንሴ ቦልድክለብ ማሠልጠኛ ሜዳው ብቻውን ልምምድ ሲያደርግ ነበር።

የብሬንትፈርድ አሠልጣኝ ቶማስ ፍራንክ ኤሪክሰን "የክለቡ ምርጥ ፈራሚ" ሊሆን ይችላል ሲሉ ተጫዋቹን ሲያስፈርሙ ተናግረዋል።

ብሬንትፈርድ ኤሪክሰንን ካስፈረመ በኋላ በጣም በርካታ የተጫዋቹ ስም የተለጠፈበት ማሊያ ቸብችቧል።

ኤሪክሰን ምንም እንኳ አደጋው ያጋጠመው ሰሞን ወደ ሜዳ ስለመመለስ ባያስብም እግር ኳስን እርግፍ አድርጎ ስለመተው ግን አስቦ እንደማያውቅ ይናገራል።

"ምንም ዓይነት አደጋ አያሰጋኝም። አይሲዲ ተገጥሞልኛል። የሆነ ነገር ቢፈጠር እንኳ ደህና ነኝ።"