የሲኤንኤን ፕሬዝዳንት ሥራቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለቀቁ

የሲኤንኤን ፕሬዚዳንት ጄፍ ዛከር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የሲኤንኤን ቴሌቪዥን ፕሬዝዳንት ጄፍ ዛከር ሥራቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለቀቁ፡፡

ሚስተር ዛከር ሥራቸው እንዲለቁ ምክንያት ተብሎ የተጠቀሰው በመሥሪያ ቤቱ ውስጥ ከነበረች ሌላ ሠራተኛ ጋር ድብቅ የፍቅር ግንኙነት ኖሯቸው ሳለ ይህንን ይፋ ሳያደርጉ በመቆየታቸው ነው፡፡

የ56 ዓመቱ ጄፍ ዛከር ‹ይህን ማድረግ አልነበረብኝም፤ ተሳስቻለሁ› ሲሉ ለባልደረቦቻቸው በተውት ማስታወሻ ጸጸታቸውን ተናዘዋል።

ጄፍ ዛከር የነበራቸው ግንኙነት ሊደረስበት የቻለው ከዝነኛው የቀድሞ የሲኤንኤን ጋዜጠኛ ክሪስ ኩሞ ጋር በተያያዘ ምርመራ በሚደረግበት ጊዜ ነው፡፡

ክሪስ ኩሞ በቅርብ ወራት በወሲባዊ ትንኮሳ ቅሌት ተጠርጥረው የተከሰሱት የኒውዮርክ ገዥ የአንድሩ ኩሞ ታናሽ ወንድም ነው፡፡

የሴኤንኤን ፕሬዝዳንት የነበሩት ሚስተር ዛከር በአሜሪካ እጅግ ኃያል ከሚባሉ የሚዲያ አለቆች አንዱ ነበሩ፡፡

ለዚህ ድብቅ የፍቅር ግንኙነት ምክንያት የሆነው ምርመራ የተጀመረው ጋዜጠኛ ክሪስ ኩሞ የቀድሞውን የኒውዮርክ ገዥ የነበሩትን ታላቅ ወንድማቸውን አንዱሩ ኩሞን በወሲባዊ ትንኮሳ ከተከሰሱ በኋላ ስማቸውን ለማደስ ያልተገባ እርዳታ አድርገዋል በሚል ነው፡፡

በዚህ የምርመራ ሂደት እግረ መንገድ የሚስተር ዛከር ድብቅ የፍቅር ግንኙነት ተደርሶበታል፡፡

የጄፍ ዛከር የስርቆሽ የፍቅር ግንኙነቱ ከማን ጋር ነበር የሚለውን ሚስተር ዛከር በይፋ ባይናገሩም መረጃዎች የፍቅር ግንኙነቱ ከአሊሰን ጎለስት ጋር እንደነበረ ያሳያሉ፡፡

አሊሰን ጎለስት ደግሞ የኔትወርኩ ምክትል ሥራ አስፈጻሚና የማርኬቲንግ ኃላፊ ነበረች፡፡

"የፍቅር ግንኙነቱን ስንጀምር መናገር ነበረብኝ፤ ያን አላደረኩም፤ ስለዚህ በገዛ ፈቃዴ ሥራ ለቅቂያለሁ፡፡" ብለዋል ጄፍ ዛከር ለባልደረቦቻቸው በተውት ማስታወሻ፡፡

ሚስተር ዛከር ከአሊሰን ጋር የነበራቸው ግንኙነት ለሁለት ዓመታት እንደዘለቀ አምነዋል፡፡

አሊሰን በበኩሏ ከጄፍ ጋር የነበራት ትውውቅ ለ20 ዓመታት የቆየ እንደነበረ ጠቅሳ "በቅርብ ዓመታት ግን ወደ ፍቅር ግንኙነት ማደጉን ሆኖም ግን ይህን ማሳወቅ ሲገባን አላደረግነውም፤ ይህም ይጸጽተኛል" ብላለች፡፡

በአንድ የሚዲያ ተቋም በሠራተኞች መካከል የፍቅር ግንኙነት ሲኖር ይፋ እንዲደረግ ይጠበቃል፡፡ ይህም የገለልተኝነትና የጥቅም ግጭት ጥያቄን ስለሚያስነሳ ነው፡፡

ጄፍ የሲኤንኤን ሥራ አስፈጻሚ ሳሉ አሊሰን የኤንቢሲ ዩኒቨርሳል ሥራ አስኪያጅ ነበረች፡፡

በ2012 አሊሰን የቀድሞ የኒውዮርክ ገዥ እና አሁን በወሲብ ቅሌት የተከሰሱት የዝነኛው የአንድሩ ኩሞ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ነበረች፡፡

ሆኖም በዚህ ሥራ ለ4 ወራት ከቆየች በኋላ ከኒውዮርክ ገዥ አንዱሩ ኩሞ የኮሚኒኬሽን ኃላፊነት በመልቀቅ ሲኤንኤንን ተቀላቅላለች።

ሚስተር ጄፍ ዛከር በበኩላቸው ሲኤንኤንን የተቀላቀሉት በአውሮጳዊያኑ 2013 ነበር፡፡

በርሳቸው አመራር ጊዜ ሴኤንኤን በታሪኩ አግኝቶት የማያውቀውን የተመልካች ብዛት ማግኘት ችሎ ነበር፡፡

በተለይም በ2020 የአሜሪካ ካፒቶል ሒል ነውጥን ተከትሎ ሲኤንኤን በአሜሪካ በከፍተኛ ደረጃ ተመልካች በማግኘት ክብረ ወሰን ሰብሮ ነበር፡፡

ሆኖም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከፍታ ነክቶ የነበረው የተመልካች ቁጥር ቁልቁል ወርዶ በታሪክ ዝቅተኛ የሚባል ደረጃ ደርሷል፡፡

ሲኤንኤን ከባለፈው ዓመት ጥር ወር የነበረው ተመልካች ከዚህ ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነጻጸር በ90 እጅ ዝቅ ብሏል፡፡

በጄፍ ዛከር ጊዜ ሲኤንኤን እጅግ የበዛ የይዘት ሽፋን ለቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በመስጠቱ ይተቻል፡፡

ዶናልድ ትራምፕም ቢሆኑ ‹ሐሳዊያን› እያሉ ከሚወነጅሏቸው የዜና አውታሮች አንዱ ይኸው ሲኤንኤን ነው፡፡

ጄፍ ዛከር ወደ ሴኤንኤን ከመምጣታቸው በፊት በኤንቢሲ ኃላፊ ነበሩ፡፡

በዚያ ወቅት ታዲያ ‹ ዘ አፕሪንቲስ› የተሰኘው የዶናልድ ትራምፕ የቴሌቪዥን እውናዊ መዝናኛ ትዕይነት (Reality show) አጽዳቂ ነበሩ፡፡