ሳዲዮ ማኔ ሴኔጋልን ለአፍሪካ ዋንጫ ፍጻሜ አደረሳት

ሳዲዮ ማኔ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

በትናንትናው ዕለት ሴኔጋል ቡርኪናፋሶን 3 ለ1 በመርታት ለሶስተኛዋ የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ ፍጻሜ አልፋለች፤ በዚህም ስኬት ከፍተኛ ሚናን የተጫወተው ሳዲዮ ማኔ ነው።

የሚገርሙ ክስተቶች ተስተናግደውበታል በተባለው ጨዋታ ሁለት ፍፁም ቅጣት ምቶች በቪዲዮ ድጋፍ አማካኝነት ሴኔጋል የተከለከለች ሲሆን በመጀመሪያውም ክስተት የቡርኪናፋሶው ግብ ጠባቂ ሄርቬ ኮፊ ተጎድቶ በፋሪድ ኦድራጎ እንዲተካ ሆኗል።

የሴኔጋሎቹ አብዱ ዲያሎ እና ኢድሪሳ ጉዬ ሴኔጋል እንድትመራ ያስቻላትን ሁለት ጎሎች ያስቆጠሩ ሲሆን የቡርኪናፋሶው ብላቲ ቱሬ አንድ ጎል በማስቆጠር ልዩነቱን ማጥበብ ችሎ ነበር።

ነገር ግን አገሩ የውድድሩ አሸናፊ የሆነችበት ጎል በሳዲዮ ማኔ ተቆጠረች።

ለማኔ ለአገሩ ያስቆጠራት 29ኛ ጎል ስትሆን ከሄንሪ ካማራም ጋር የምንግዜም ጎል አስቆጣሪዎች በሚል በአንደኛ ደረጃነት እንዲቀመጥ አድርጎታል።

እሁድ በሚጠናቀቀው በአፍሪካ ዋንጫ ሴኔጋል፣ ግብፅን ወይም ካሜሩንን ትገጥማለች።

ቡርኪናፋሶ ለሶስተኛነት ወይም ለአራተኛነት በሚደረገው ፍልሚያ በመጪው ቅዳሜ ጨዋታዋን ታደርጋለች።

"ይህ የደረስንበትን ወቅት ያሳያል። በሁለት ተከታታይ የአፍሪካ ዋንጫ ፍፃሜ መድረስ ቀላል እንደማይሆን እናውቅ ነበር፤ ነገር ግን አድርገነዋል። በአሁኑ ወቅት ለኛ መሰረታዊው ጉዳይ ማንም ይሁን ማን ይግጠመን ተፋልመን ማሸነፍ ነው" ብሏል ማኔ።

ማኔ የቡርኪናፋሶ ቡድን በጣም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደነበርና በጣም ከብዷቸውም እንደነበር አልደበቀም።

"በጣም ከባድ ጨዋታ ጠብቀን ነበር። አዎ ፈታኝ ነበር፤ ነገር ግን ተረጋግተን ብዙ እድሎችን ፈጥረናል። ማሸነፍ ይገባናል ብዬም አስባለሁ" በማለት ተናግሯል።

"ምን ያህል ደስተኛ እንደሆንኩኝ ፊቴ ላይ የምታዩት ይመስለኛል፣ ይህ ለኔ የተለመደ ነው። በግሌ እኮራለሁ፣ እናም ለራሴ፣ ለቡድን ጓደኞቼ እና ለአገሬ በጣም ደስተኛ ነኝ።" ብሏል ማኔ

የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን

የፎቶው ባለመብት, Reuters