በሞሪሺየስ አውሮፕላን መጸዳጃ ቤት ውስጥ አራስ ልጅ ተጥሎ ተገኘ

ታትሟል

ሞሪሺየስ ውስጥ የሚገኝ አየር ማረፊያ ሠራተኞች በአንድ አውሮፕላን መጸዳጃ ቤት የቆሻሻ መጣያ ውስጥ አራስ ልጅ ተጥሎ ማግኘታቸው ተነገረ።

ተጥሎ የተገኘውን አራስ ልጅ በበረራ ላይ ሳለች ወልዳ ጥላዋለች የተባለች አንዲት የ20 አመት ማዳጋስካራዊት ሴት ተጠርጥራ በቁጥጥር ስር ውላለች።

ከማዳጋስካር ተነስቶ በሞሪሺየስ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ቅዳሜ ዕለት በደረሰው የኤር ሞሪሺየስ አውሮፕላን ውስጥ ነው ጨቅላው የተገኘው።

የአየር ማረፊያው ሠራተኞች አራሱን ልጅ ያገኙት የተለመደውን ፍተሻ በአውሮፕላኑ ላይ ሲያደርጉ መሆኑም ተገልጿል።

ሠራተኞቹ በመጸዳጃ ቤቱ የጽዳት ወረቀቶች ላይ ደም በመመልከታቸው ተጥሎ ያገኙት ጨቅላ የህክምና እርዳታ እንዲያገኝ ወደ ሆስፒታል በአፋጣኝ ወስደውታል።

የጨቅላው ተጥሎ መገኘትን ተከትሎ የአየር ማረፊያው ፖሊሶች እናቱን ለማግኘት መንገደኞች ላይ ምርመራ ማድረጋቸው ተነግሯል።

መጀመሪያ ላይ ጨቅላው የእሷ መሆኑን አስተባብላ የነበረች የህጻኑ እናት ናት ተብላ የተጠረጠረች ሴት የህክምና ምርመራ ካደረገች በኋላ ተጥሎ የተገኘው አራስ ልጅ እናት መሆኗ ተረጋግጧል።

ከዚህ በኋላም በፖሊስ ጥበቃ ስር ሆና የህክምና ክትትል እንድታገኝ የተደረገ ሲሆን፤ በአሁኑ ጊዜ እሷም ሆነች ጨቅላ ልጇ በጥሩ የጤንነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።

የሁለት ዓመት የሥራ ፈቃድ ይዛ ወደ ሞሪሺየስ የገባችው ማዳጋስካራዊቷ እናት የህክምና ክትትሏን ከጨረሰች በኋላ በፖሊስ ምርመራ የሚደረግባት ሲሆን፣ አራስ ልጅ በመጣልም ክስ ይመሰረትባታል ተብሏል።