ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቡሊ ባይ፡ ሙስሊም ሴቶችን 'ለሽያጭ' ያቀረበው የሕንድ መተግበሪያ ተዘጋ
በሕንድ አንድ መተግበሪያ 'ለሽያጭ የቀረቡ' ሲል ከ100 በላይ የሚሆኑ ሙስሊም ሴቶችን ፎቶ ካጋራ በኋላ ፖሊስ በሁለት የአገሪቷ ግዛቶች ክስ አቀረበ።
ከተከሳሾቹ መካከል ምሥሎችንና ይዘቶችን ያጋሩ የመተግበሪያው አበልጻጊዎች እና የትዊተር ባለቤቶች ይገኙበታል።
'ቡሊ ባይ' የተባለው መተግበሪያው እስከሚዘጋ ድረስ 'ጊትሀብ' በሚባል ድረ ገጽ አማካኝነት ይሠራ ነበር።
በኢንተርኔት አማካይነት በሕንድ ሙስሊም ሴቶችን ለመሸጥ ሙከራ ሲደረግ በወራት ውስጥ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
ሐምሌ ወር ላይ 'ሱሊ ዲልስ' የተባለ መተግበሪያና ድረ ገጽ ሴቶቹ በኦንላይን ላይ የጫኗቸውን ፎቶግራፎች በመጠቀም ከ80 በላይ ለሚሆኑ ሙስሊም ሴቶች ፕሮፋይል በመክፈት "በዕለቱ ለሽያጭ የቀረቡ" ሲል ይፋ አድርጎ ነበር።
ይሁን እንጂ በሁለቱም መተግበሪያዎች የተከናወነ ትክክለኛ ሽያጭ የለም። ይህንን የሚያደርጉበት ዋና ዓላማ ሙስሊም ሴቶችን ፎግራፎቻቸውን በማጋራት ማንኳሰስ እና ማዋረድ ነው።
'ሱሊ' የሚለው ቃል የሂንዱ ቃል ሲሆን የቀኝ ክንፍ ሂንዱ አክራሪዎች ሙስሊም ሴቶችን ለማዋረድ የሚጠቀሙበት ቃል ነው። 'ቡሊ' ማለትም በተመሳሳይ ሙስሊም ሴቶችን የሚያንኳስስ ቃል ነው።
ስሟ እና ፎቶግራፏ በቡሊ ባይ መተግበሪያ ላይ የሰፈረው ጋዜጠኛ ኢስማት አራ ባሳለፍነው ቅዳሜ እና እሁድ ቅሬታዋን ዴልሂ ለሚገኘው ፖሊስ ክስ አቅርባ ነበር።
ክሱ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ላይ የቀረበ ሲሆን በሐይማኖት ምክንያት ጾታዊ ትንኮሳ እና ጠላትነት መፍጠርን ይጨምራል።
በቡሊ ባይ ዝርዝር ላይ ባለች ሌላ ሴት በቀረበ ቅሬታ መሠረትም የሙምባይ ፖሊስ በርካታ የትዊተር ባለቤቶችና መተግበሪያውን በሰሩት ላይ ሁለተኛ ክስ አቅርቧል።
በክሱ በርካታ ጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶች፣ ሽልማት ያገኘ የቦሊውድ ተዋናይ እና በ2016 የጠፋች የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እናት ይገኙበታል።
በመተግበሪያው ላይ ፎቶግራፋቸው የቀረቡ ሴቶች ፍርሃት እንደተሰማቸውና እንደተሳቀቁ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
ይሁን እንጂ በሱሊ ዲልስ ላይ ክስ ከቀረበ ከስድስት ወር በላይ ቢሆንም ፖሊስ በቁጥጥሩ ሥር ያዋለው አካል የለም።
ጋዜጠኛዋ አስራ ለአልጀዚራ እንደተናገረችው በፖሊስ ምርመራ ላይ ውጤት አለመታየቱ መተማመንን አልፈጠረም ብላለች።
የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስተር አሽዊን ቫይሽናው ቅዳሜ ዕለት ጊትሀብ የተባለው ድረ ገጽ መተግበሪያውን የሚጭኑ ሰዎችን እንዳገዳቸው ገልጸዋል።
ከዚህም ባሻገር ተጨማሪ እርምጃ ለመውሰድ ፖሊስ በኢንተርኔት ጉዳይ ላይ ከሚሰሩ ተቋማት ጋር እየሰራ ነው ብለዋል- ሚኒስትሩ።
የሺቭ ሴና ፓርቲ የሕግ አውጪ የሆኑት ፕሪያንካ ቻቱረቨድ በዚሁ ጉዳይ ላይ በትዊተር ገጻቸው ምላሽ ሰጥተው ነበር።
ሕግ አውጪዋ "እንደዚህ ዓይነት ድረ ገጾችን ከመዝጋት በተጨማሪ ይህንን የሚፈጥሩ ወንጀለኞችን መቅጣት ወሳኝ ነው" ብለዋል።
ፕሪያንካ አዲሱን መተግበሪያ የተፈጠረው ሱሊ ዲልስን የሰሩት ስላልተቀጡ ነው ሲሉም ለኤኤንአይ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
የሴቶች ብሔራዊ ኮሚሽን ሊቀመንበርም የዴልሂ ፖሊስ በጉዳዩ ላይ ስለወሰደው እርምጃ እንዲያሳውቅ በትዊተር ገጻቸው ጠይቀዋል።
የማሃራሽትራ ግዛት የአገር ውስጥ ሚኒስተር ሳቴጅ ፓቲል በበኩላቸው እንደ ጊትሃብ ያሉ ዲጂታል መድረኮችን "አሳሳቢ እና በጥላቻ የተሞሉ" ሲሉ ተችተዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም የፌደራል ፖሊስ በሱሊ ዲልስ ጉዳይ ላይ የደረሰበትን የምርመራ ውጤት እንዲያሳውቅ ጠይቀዋል።
በ2018 አምነስቲ ኢንተርናሽናል በሕንድ ስላለው የኢንተርኔት ላይ ትንኮሳን በተመለከተ ባወጣው ሪፖርት፤ ሴቶች ድምጻቸው በተሰማ ቁጥር ኢላማ የመሆን እድላቸው የሰፋ እንደሚሆን አመልክቷል።
ይህ ደግሞ አንድን ሐይማኖት በሚከተሉ አነስተኛ ቁጥር ባላቸው ሰዎች እና የተገለሉ ጎሳዎች ላይ የከፋ ነው ብሏል -ሪፖርቱ።