ከደቡብ አፍሪካ ፓርላማ ቃጠሎ ጋር በተያያዘ አንድ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በደቡብ አፍሪካ ኬፕ ታውን ከተማ የሚገኘውን የደቡብ አፍሪካ ፓርላማ ውስጥ ከተነሳው ከፍተኛ የእሳት አደጋ ጋር የተጠረጠረ አንድ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ።
የፖሊስ ቃል አቀባይ እንዳለው ግለሰቡ እሳት ቃጠሎ በማስነሳት፣ ቤት ሰበሮ በመግባት እና በዝርፊያ ወንጀል ክስ እንደቀረበበት እና ነገ ማክሰኞ ፍርድ ቤት እንደሚቀርብም ተገልጿል።
የእሳት አደጋ ሠራተኞች እሳቱን ለማጥፋት ለሰዓታት ሲረባረቡ ቆይተዋል።
ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ የፓርላማው ሥራ እንደሚቀጥል በመግለጽ ጉዳዩን "አሰቃቂ እና አውዳሚ ክስተት" ብለውታል። ትላንት እሁድ ከስፍራው የወጡ ምስሎች ላይ ከፓርላማው ህንጻው ጣሪያ ላይ ከፍተኛ የእሳት ነበልባል እና ጭስ ታይቷል።
እሳቱ ሦስተኛ ፎቅ ላቅ ካሉ ቢሮዎች በመነሳት በፍጥነት ወደ ብሔራዊ ምክር ቤት (የፓርላማው የታችኛው ምክር ቤት) ክፍል መዛመቱን በኬፕ ታውን የቢቢሲ ዘጋቢ ኖምሳ ማሴኮ ባለሥልጣናትን ጠቅሳ ዘግባለች።
ፓርላማው በአሁኑ ጊዜ በበዓል ምክንያት ለእረፍት መበተኑን ተከትሎ በቃጠሎው ወቅት በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት የለም ተብሏል።
ፓርላማው እሁድ ምሽት በሰጠው መግለጫም፤ የሕግ አውጪዎች በሚሰበሰቡበት የብሔራዊ ምክር ቤት ክፍልን ጨምሮ በህንፃው አዲስ ምክር ቤት ክንፍ ላይ "ከፍተኛ ጉዳት" መድረሱን አረጋግጧል። አንዳንድ መሥሪያ ቢሮዎችም "በከባድ ሁኔታ ተቃጥለዋል" ብለዋል።
ቃጠሎው የጀመረው ከቀኑ 6፡00 ሰዓት በኋላ የሊቀ ጳጳስ ዴዝሞንድ ቱቱ የቀብር ሥነ ሥርዓት በፓርላማ አቅራቢያ በሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል በተካሄደ ማግሥት ነው።
ከቃጠሎው በኋላ በስፍራው የተገኙት ፕሬዘዳንት ራማፎሳ፤ የእሳቱ ዜና "ከአንድ ቀን በፊት ወደ ነበርንበት ሐዘን የሚመልስ፤ ሊቀ ጳጳስ ቱቱም ይህንን ቢያዩ በጣም ያዝኑ ነበር" ብለዋል።
የሕንፃው የእሳት አደጋ ጊዜ የውሃ ርጭት መስመር ባግባቡ አለመዘርጋቱን የገለጹት ፕሬዜዳነቱ፤ የእሳት አደጋ ተከላካዮች በደቂቃዎች ውስጥ ምላሽ በመስጠታቸው አወድሰዋል።
የኬፕ ታውን ከንቲባ የደህንነት ኮሚቴ አባል የሆኑት ዣን ፒየር ስሚዝ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ከአሮጌው የመሰብሰቢያ አዳራሽ በላይ ያለው ጣሪያ ሙሉ በሙሉ መውደሙን ብሎም በውስጡ የደረሱ ተጨማሪ ጉዳቶች እስካሁን አልተለዩም ።
"በውስጡ የደረሰውን ጉዳት ለመመልከት አሁን አይተቻለም። ነገር ግን ብዙ ታሪካዊ ቅርሶች ስላሉት ውድመቱ ቀላል እንዲሚሆን ተስፍ እናደርጋለን። በሮቹን ካልሰበርን በስተቀር ያንን መመልከት ስላልቻልን እና እሱን ማድረግ ስላልፈለግን እንጠብቃለን" በማለት ገልጸዋል።
የፓርላማው የእሳት አደጋ ማንቂያ ደወል የጮኸው የእሳት አደጋ ባለሞያዎች በስፍራው ከደረሱ በኋላ እንደሆነም አክለዋል።












