እስራኤል 5 ሺህ አዕዋፋትን የገደለውን 'የአቪያን ፍሉ' ወረርሽኝ ለመቆጣጠር እየጣረች ነው

ከ5,000 በላይ የሚሆኑ እና የሚፈልሱ 'ክሬንስ' ተብለው የሚታወቁ የአዕዋፍት ዝርያዎች ሞተዋል።

የፎቶው ባለመብት, ISRAEL NATURE AND PARKS AUTHORITY

ታትሟል

በእስራኤል ከባዱና የአዕዋፋት ዝርያን የሚያጠቃው የአቪያን ፍሉ ወረርሽኝ መቀስቀሱን ተከተሎ አገሪቱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ተርኪ የተባሉ የዶሮ ዝርያዎችን እያስወገደች ነው።

የአገሪቱ አካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር ታማር ዛንድበርግ፤ በእስራኤል ታሪክ ውስጥ "በዱር እንስሳት ላይ የከፋ ጉዳት" ሲሉ በገለጹት ወረርሽኝ ሳቢያ በሁላ የተፈጥሮ ጥብቅ ስፍራ ከ5,000 በላይ የሚሆኑ እና የሚፈልሱ 'ክሬንስ' ተብለው የሚታወቁ የአዕዋፋት ዝርያዎች ሞተዋል።

የአገሪቱ አርሶ አደሮችም ወረርሽኙን ለመከላከል በሚል ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ ተርኪ ዶሮዎችን እንዲያስወግዱ እየተገደዱ ሲሆን፤ ይህም በእስራኤል የእንቁላል እጥረት ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።

እስካሁን ይህ አዕዋፋቱን የሚያጠቃው ቫይረስ ወደ ሰው ስለመተላለፉ አልተረጋገጠም።

ሆኖም የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ናታሊ ቤኔት በሽታው ወደ ሰዎች እንዳይተላለፍ በሚደረገው ጥረት ዙሪያ ለመወያየት ሰኞ ዕለት የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪያቸውን እና ሌሎች ባለሙያዎችን ማነጋገራቸው ተሰምቷል።

በበሽታው ከተያዙ አዕዋፋት ጋር የቅርብ ግንኙነት ወይም ንክኪ የነበራቸው ሰዎች የመከላከያ ሕክምና እየተደረገላቸው ነው።

አቪያን ፍሉ ከአዕዋፋት ወደ ሰው የመተላለፍ ዕድሉ ጠባብ ቢሆንም እንደ አውሮፓውያኑ ከ2003 ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ 456 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መሞታቸውን የዓለም ጤና ድርጅት አሳውቋል።

ከእስራኤል ተፈጥሮ እና ፓርኮች ባለሥልጣን የወጡ ምስሎች፣ ሌሎች የዱር እንስሳት በወረርሽኙ እንዳይያዙ ለመጠበቅ ከሁላ ሐይቅ የሞቱ ክሬኖችን ለማንሳት የተሰማሩ ባለሙያዎችን ያሳያል።

ሁላ በተሰኘው ጥብቅ ስፋራ ዙሪያ ባለው ሸለቆ ውስጥ የ250 ክሬኖች ቅሪቶች መታየታቸውን እና 30ዎቹ ደግሞ ታመው በአገሪቱ ሌላ ስፍራ መታየታቸውንም ባለሥልጣኑ ገልጿል።

ከአውሮፓ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ እነዚህ አዕዋፋት በሁላ የተፈጥሮ ጥበቅ ስፍራ ላይ ሲከርሙ ማየት ብዙውን ጊዜ ለወፍ አድናቂዎች አስደሳች ክስተት ነው። ነገር ግን ጣቢያው ባለፈው ሳምንት ለጎብኝዎች ዝግ የተደረገ ሲሆን ምክንያቱ ድግሞ ከባድ እንደሆነ የተገለጸው በአቪያን ፍሉ ወረርሽኝ ነው።

ምልክቶች የማይታዩበት አቪያን ፍሉ በባሕርያቸው ከቦታ ቦታ በሚፈልሱ ወፎች ላይ የሚከሰት ነው።

በአገር ውስጥ ያሉ ወፎች ለዚህ ወረርሽኝ ያላቸው ተጋላጭነት ዝቅተኛ ቢሆንም ቫይረሱ ለሽያጭ በቀረቡ ወይም በቤተሰብ ውስጥ በሚራቡ የአዕዋፍ ዝርያዎች ላይ ከተገኘ ግን ሁሉንም በፍጥነት ማስወገድ ይመከራል።

በሰሜን እስራኤል 12 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ሞሻቭ ማርጋዮት በተሰኘው የጋራ ማርቢያ ውስጥ ከግማሽ ሚሊዮን የሚበልጡ እንቁላል የሚጥሉ ዶሮዎች ወረርሽኙን ለመቆጣጠር እና በሰዎች ላይ ያለውን አደጋ ለመቀነስ እየተገለሉ መሆኑን የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ሞሻቭ በእስራኤል ውስጥ ጥቅም ላይ ከሚውሉ እንቁላሎች 7 በመቶውን ያቀርባል።

ታይምስ ኦፍ እስራኤል የተሰኘው ሚዲያ እንደዘገበው በእስራኤል የመጀመሪያው የአቪያን ፍሉ ወረርሽኝ እንደ አውሮፓውያኑ ጥቅምት 18 ተመዝግቧል።