ኢንዶኔዥያ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ላይ ጥላ የነበረውን እገዳ አነሳች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ኢንዶኔዥያ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ላይ ጥላ የነበረውን እገዳ አነሳች።
የላየን ኤር አየር መንገድ ከሦስት ዓመታት በፊት 189 ሰዎች የሞቱበት የአውሮፕላን መከስከስ ከገጠመው በኋላ የቦይንግ ማክስ 737 አውሮፕላኖች እንዳይበሩ ተከልክሎ ነበር።
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ አየር መንገድም ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖችን ከአንድ ወር በኋላ ወደ በረራ ለመመለስ በመጨረሻው የዝግጅት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ መግለጹ ይታወሳል።
በመጋቢት 2011 ዓ. ም. የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ተከስክሶ 149 መሞታቸውን ተከትሎ ቦይንግ 737 ማክስ ከበረራ ታግዶ ቆይቷል።
አሜሪካ እና የአውሮፓ አገራት 737 ማክስ አውሮፕላን ወደ በረራ እንዲመለስ ከፈቀዱ ወራት ተቆጥረዋል።
ዘንድሮ አውስትራሊያ፣ ጃፓን፣ ሕንድ፣ ማሌዥያ እና ሲንጋፖር 737 ማክስ ላይ የጣሉትን እገዳ ያነሱ ሲሆን፤ እስካሁን ባጠቃላይ 180 አገራት ለ737 ማክስ ፈቃድ ሰጥተዋል።
የኢንዶኔዥያ የትራንስፖርት ሚኒስቴር እንዳለው፤ በ737 ማክስ የደኅንነት መቆጣጠሪያ ላይ ፍተሻ መካሄዱን ተከትሎ አውሮፕላኑ በቅርቡ ወደ በረራ እንዲመለስ ተወስኗል።
አየር መንገዶች 737 ማክስ አውሮፕላኖቻቸውን ከማብረራቸው በፊት መከተል ያለባቸውን የፍተሻ መመሪያ ተደንግጓል። መንግሥትም ፍተሻ የሚያካሂድ ይሆናል።
ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኑ የተከሰከሰበት ላየን ኤር 10 ማክስ አውሮፕላኖች ያሉት ሲሆን፤ አውሮፕላኖቹ ወደ በረራ እንዲመለሱ ከተወሰነ በኋላ ከቢቢሲ አስተያየት ቢጠየቅም እስካሁን ምላሽ አልተኘም።
በኢንዶኔዥያ መንግሥት የሚተዳደረው ጋሩዳ አየር መንግድ በበኩሉ አሁን ላይ ዋነኛ ትኩረቱ ያለበትን ዕዳ ማቃለል እንደሆነና 737 ማክስ አውሮፕላንን ወደ በረራ የመመለስ ዕቅድ እንደሌለው ገልጿል።
እገዳው ከመጣሉ በፊት አየር መንገዱ አንድ 737 ማክስ አውሮፕላኑ ብቻ ነበር እየተንቀሳቀሰ የነበረው።
አየር መንገዱ ወጭ ለመቀነስ ሲል የሚያበራቸውን አውሮፕላኖች ከ144 ወደ 66 መቀነሱንም አስታውቋል።
እአአ በ2018 የላየን ኤር አየር መንገድ የበበራ ቁጥር 610 አውሮፕላን ከጃካርታ ተነስቶ ጉዞ ማድረግ በጀመረ በ13 ደቂቃ ውስጥ ነበር ወድቆ የተከሰከሰው።
ከአምስት ወር በኋላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር ኢቲ 302 ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ለመብረር ከተነሳ ከደቂቃዎች በኋላ ከአዲስ አበባ ወጣ ብሎ መከስከሱ ይታወሳል።
በሁለቱ አደጋዎች በአውሮፕላኖቹ ውስጥ የነበሩ ሁሉም 346 ሰዎች ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን ቦይንግ ለሟቾቹ ቤተሰቦች በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ካሳ እንዲከፍል ተጠይቋል።
አደጋዎቹን ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ላየን ኤር ብቻ ሳይሆኑ በዓለም ዙሪያ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ካለባቸው የደኅንነት መቆጣጠሪያ ችግር ጋር በተያያዘ በረራ እንዲያቆሙ ተደርገው ቆይተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ተወልደ ገብረማሪያምን ጠቅሶ ባወጣው መግለጫ፤ አየር መንገዱ ከሁሉም በፊት ቅድሚያ የሚሰጠው ለደኅንነት መሆኑን በመግለጽ አውሮፕላኖቹ ወደ አገልግሎት ሊመለሱ መሆኑን ገልጿል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ 737 ማክስ ወደ በረራ ለመመለስ የወሰነው በዓለም ዙሪያ ያሉ የበረራ ደኅንነት ተቆጣጠሪ አካላት ቦይንግ 737 ማክስ ለበረራ ብቁ ነው ብለው አስፈላጊውን ፈቃድ ከመስጠታቸው በተጨማሪ "በዓለም ዙሪያ ያሉ ሌሎች 34 አየር መንገዶች አውሮፕላኑን ወደ በረራ መመለሳቸውን ተከትሎ ነው" ብሏል።












