የደቡብ አፍሪካ ፍርድ ቤት ሼል እያደረገ ያለውን የነዳጅ ፍለጋ አገደ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ግዙፉ የነዳጅ ኩባኒያ ሼል በደቡብ አፍሪካ ምሥራቃዊ የባሕር ዳርቻዎች ላይ የሚያደርገውን የነዳጅ ፍለጋ እንዲቆም ፍርድ ቤት ትዕዛዝ የሰጠ ሲሆን ጉዳዩ የጨረሻ ውሳኔ እስከሚያገኝም እየተጠበቀ ይገኛል።
የነዳጅ ፍለጋው በባሕር ውስጥ ያሉ ነፍሳትን ይጎዳል በሚል ሲከራከሩ የቆዩት የአካባቢ ደኅንነት ተቆርቋሪዎች በውሳኔው ደስታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ። ሼል በበኩሉ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ እንደሚያከብር እና እና ፍለጋውንም ለጊዜው ማቆሙን ገልጿል።
የደቡብ አፍሪካ የኢነርጂ ሚኒስቴር ግዌዴ ማንታሼ በፕሮጀክቱ ላይ ተቃውሞ ያስነሱ አካላትን አፍሪካ የኃይል ሃብቷን እንዳትጠቀም ለማድረግ አላማ ይዘው ተነስተዋል ሲሉ ተችተዋል።
እግዱን ያወጣው ችሎትም ሼል በባሕር ዳርቻው አካባቢ ነዳጅ እንዲፈልግ ፈቃዱን ያገኘበት አካሄድ ያልጠራ እና አጠራጣሪ ሂደቶችን የያዘ ነው ብሏል።
በምሥራቃዊ ኬፕ ግዛት ውስጥ የሚገኘው እና ወደ 250 ኪሎ ሜትር ገደማ የሚረዝመው የባሕር ዳርቻ በተፈጥሯዊ ውበቱ ብሎም በውስጡ በያዘው የባሕር ሃብት ዝናን ያተረፈ ነው። ፍለጋውን የተቃወሙ ሰዎች እንዳሉት ይህ ፍለጋ እንደ ዶልፊን ያሉ የባሕሩ ውስጥ እንስሳትን የሚጎዳ ነው።
እንዲሁም በክሱ ውስጥ የተካተቱት የአካቢው ነዋሪዎች እንዳሉት በአካባቢው ያላቸው የመሬት ባለቤትነት እና አሳ የማጥመድ መብቶች አልተከበሩላቸውም።
"እኛ የአካባቢው ነዋሪዎች ለበርካታ መቶ ዓመታት በባሕሩ ላይ ተመስርተን ነው የኖርነው። ፍርድ ቤቱ ለአጭር ጊዜ ትርፍ ሲባል የባሕራችን ህይወት መስዋዕት መሆን እንደሌለበት እውቅና በመስጠቱ ተደስቻለሁ" ስትል የባሕር ዳርቻው ነዋሪ ኖህሌ ምቡቱባ ተናግራለች።
በስድስት ሺህ ስኩየር ኪሎ ሜትር ውስጥ የሚደረገው ይህ ፍለጋ እንዲቀጥል ከዚህ ቀደም በተደረገ የፍርድ ቤት ክርክር መፈቀዱን ተከትሎ ሼል ከአንድ ወር በፊት ፍለጋውን ለመጀመር ጥናት ጀምሮ ነበር።
ምንም እንኳን የቀድሞው ፍርድ ቤት አመልካቾች በአካባቢ ጥበቃ ላይ ፕሮጀክቱ ስለሚያመጣው ጫና በቂ ማስረጃ አላቀረቡም ቢልም፣ ማክሰኞ ዕለት የተሰጠው ፍርድ ግን ባለሞያዎች ፍለጋው የሚያስከትለውን ጉዳት የተመለከተ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፤ እንዲሁም ሼል በበቂ ሁኔታ አላስተባበለም ሲል ፕሮጅክቱን አግዶታል።
የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቿ ካትሪን ሮቢንሰን ውሳኔው "ትልቅ ድል ነው፤ ነገር ግን ትግሉ አልተገባደደም" ስትል ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል ተናግራለች።












