ናሚቢያ፡ የሀይድሮጅን ምርት ኃያል አገር ለመሆን እየሠራች ያለችው አፍሪካዊት አገር

ናሚቢያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በደቡባዊ ናሚቢያ የምትገኘው ሉደሪትዝ የወደብ ከተማ በአንድ ወቅት ከአልማዝ ሽያጭ እንዲሁም ከዓሣ ማስገር ከፍተኛ ጥቅም ታገኝ የነበረች ስትሆን፣ አሁን ግን የድሮዎቹ መሠረተ ልማቶች መፈራረሳቸውን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ ሥራ አጥነት ተንሰራፍቶባታል።

አሁን ደግሞ የሉደሪትዝ ሦስተኛው አብዮት የተባለለት አረንጓዴ የሀይድሮጂን ፕሮጀክት ብዙ ተስፋ ተጥሎበታል።

የከተማዋ ምክር ቤት አባል የሆኑት ፊሊፕ ባልሆዋ ይህ ፕሮጀክት የከተማዋን ነዋሪዎች በማሠልጠን አዲስ የሥራ እድል እንደሚከፍትላቸው ተስፋ ያደርጋሉ።

ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ የሚሳካም ከሆነ የከተማዋን የሥራ አጥ ቁጥርን በ55 በመቶ ይቀንሰዋል ተብሎ ይጠበቃል።

"ላለፉት 15 ዓመታት በኢኮኖሚው ዘርፍ ስትፈተን ለቆችው ከተማ መሰል ፕሮጀክቶች በነዋሪው ዘንድ ከፍተኛ መነቃቃትና ተስፋን የሚፈጥር ነው" ይላሉ።

ይህ ፕሮጀክት ሳው ተብሎ በሚጠራውና ለከተማዋ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘው አካባቢ የሚጀመር ሲሆን በየዓመቱ 300 ሺህ ቶን አረንጓዴ ሀይድሮጂን እንደሚያመርት ይጠበቃል።

በቀላል አማርኛ ፕሮጀክቱ ታዳሽ የሆነውን የፀሐይ ኃይል እና ንፋስን በመጠቀም ጨው ከተወገደለት የባሕር ውሃ ውስጥ የሀይድሮጂን ሞለኪውሎችን መለየት ነው።

ታዲያ በዚህ መልኩ የሚሰበሰበው ሀይድሮጂን ቀጣይነት ባለው መልኩ የኃይል ምንጭ መሆን እንደሚችል እየተነገረለት ነው።

ፕሮጀክቱን ለመጀመር ጨረታውን ያሸነፈው 'ሃይፈን ሀይድሮጂን ኤነርጂ' የተባለው ድርጅት ዝግጅቱን አጠናቆ በአውሮፓውያኑ 2026 ሀይድሮጂን ማምረት የሚጀምር ሲሆን ለሚቀጥሉት 40 ዓመታት በዚሁ ሥራ ላይ እንደሚቆይ ይጠበቃል።

ድርጅቱ እንደሚለው ፕሮጀክቱን ለማስጀመር የሚካሄደው ግንባታ እስከ አራት ዓመት ድረስ ሊፈጅ የሚችል ሲሆን 15 ሺህ ሰዎች ደግሞ በቀጥታ ሥራ ያገኙበታል።

ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገባ ደግሞ ተጨማሪ 3 ሺህ ሰዎች ሥራ እንደሚያገኙ ይጠበቃል።

ከሚፈጠሩት የሥራ ዕድሎች ደግሞ 90 በመቶ የሚሆነውን የሚይዙት የአካባቢው ነዋሪዎች ናቸው።

ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቀው የሀይድሮጅን ማምረቻ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቀው የሀይድሮጅን ማምረቻ

ጄምስ ምንዩፔ የናሚቢያ መንግሥት የኢኮኖሚ ዘርፍ አማካሪ እንዲሁም የሀይድሮጂን ኮሚሽነር ናቸው።

እሳቸው እንደሚሉት የሉደሪትዝ ከተማ ለመሰል ፕሮጀክቶች ተመራጭ የሆነ አቀማመጥ ነው ያላት።

ለባሕር ቅርብ መሆኗ፣ የፀሐይ ብርሃን መገኘቱ እንዲሁም አካባቢው ነፋሻማ መሆኑ ነው ለፕሮጀክቱ ተመራጭ ያደረጋት ከተማዋን።

በተጨማሪ ደግሞ ከተማዋ የወደብ አገልግሎትም መስጠቷ ትልቅ ግብዓት ነው።

አማካሪው እንደሚሉት ይህ የሀይድሮጂን ፕሮጀክት የናሚቢያው ፕሬዝደንት ሄግ ጌይንጎብ ዕቅድ አካል ነው።

"ፕሬዝደንቱ የአካባቢውን ኢኮኖሚ የሚያነቃቃና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊ የሚሆን እንዲሁም ቀጣይነት ያለው ዘርፍ የመገንባት እቅድ አላቸው" ይላሉ።

ከሀይድሮጂን ፕሮጀክቱ የሚገኘው ገቢ ደግሞ የግብርና፣ የሎጂስቲክስ እና የኃይል አቅርቦት ዘርፎችን ለመደገፍ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይጠበቃል።

በተጨማሪም የሀይድሮጅን ታዳሽ ኃይል ለባቡር አገልግሎት ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል ሲሆን ለጎረቤት አገራትም ለመላክ ታስቧል።

ይህ ታዳሽ ኃይል የአገሪቱን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ለማሟላት ትልቅ ሚና ሊኖረው እንደሚችል ይታመናል።

በተጨማሪም አገሪቱ ከደቡብ አፍሪካ የምታስገባውን የድንጋይ ከሰል መጠን በእጅጉ እንደሚቀንሰው ይጠበቃል።

በዚህ ረገድ ናሚቢያ ለምታካሂደው መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ ድጋፎችን ለማሰባሰብ ከጀርመን፣ ከቤልጂየም እና ከኔዘርላንድስ ጋር ስምምነት ተፈርሟል።

ፕሮጀክቱም በአጠቃላይ እስከ 9.4 ቢሊየን ዶላር እንደሚያስፈልገው ተገልጿል።

ይህ ገንዘብ ከፍተኛ ነው።

በአውሮፓውያኑ 2020 የናሚቢያ አጠቃላይ አገራዊ ምርት 10.7 ቢሊየን ዶላር ነበር።

ሀከላይ የተጠቀሰውን ገንዘብ ለፕሮጀክቱ ለማሰባሰብ ደግሞ ከነዚህ አገራት የሚገኘው ድጋፍ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።