"ለሕይወታችን እንፈራለን"- ከደቡብ አፍሪካ ለቅቀው እንዲወጡ ቀን የተቆረጠላቸው ስደተኞች

የፎቶው ባለመብት, Thuthuka Zondi / BBC
ደቡብ አፍሪካ ለስደተኞች የጥቃት ስፋራ ሆናለች።
በደቡብ አፍሪካ ስደተኞች አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ በተቃዋሚዎች የተቆረጠው ቀን እየተቃረበ መሆኑን ተከትሎ ስጋት ነግሷል።
የማሊ ዜጋ የሆነችው የ36 ዓመቷ እስናት ጆሴፍ እያለቀሱ የነበሩ የአንድ ዓመት ሦስት መንታ ልጆቿን እያባበለች "በጣም ፈርቻለሁ፤ ተጎድቻለሁ" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።
በወደብ ከተማዋ ደርባን ኢ መደበኛ በሆነ ሰፈራ ትኖርበት የነበረውን ቤቷን ለቅቃ ለመውጣት ተገዳለች። ሰባት ሺህ የሚሆኑ በአብዛኛው ማሊያውያን የሆኑ ስደተኞች እስከ እቃዎቻቸው ከሁለት ሳምንታት ጀምሮ ባዶ ሜዳ ላይ ወድቀዋል።
"ሰዎች ቤቴ መጥተው 'መልቀቅ አለብሽ። እናንተ ሰዎች ከዚህ በላይ እዚህ እንድትሆኑ አንፈልግም። ስለዚህ ወደ አገርሽ ተመልሰሽ መሄድ አለብሽ' አሉኝ። አስር ነበሩ፤ መሣሪያ ይዘዋል" ትላለች በቡድን ቆንጨራ እና አለንጋ ይዘው የመጡ ደቡብ አፍሪካውያንን ስትገልፅ።
"ባለቤቴን ራሱን እና አንገቱን በስለት ጎዱት። አንገቱን ለመግደል እንደፈለጉ አድርገው ይዘውት ነበር። በእግዚአብሔር ምክንያት ተርፏል፤ ነገር ግን ሆስፒታል ነው።"
የረድኤት ድርጅቶች ብርድ ልብስ እና ምግብ እየሰጧቸው ያሉት በሜዳው የተጠለሉ አብዛኞቹ ስደተኞች በመኖሪያ ቤታቸው ሳሉ ተመሳሳይ ዛቻ ደርሶባቸዋል።
'ማርች ኤንድ ማርች'፣ ተቃዋሚ ፓርቲው 'አክሽን ሳውዝ አፍሪካ' እና ሌሎችም ፀረ ስደተኛ ተቃዋሚዎች በአመዛኙ ሰላማዊ የተባለ ተቃውሞ ካደረጉ በኋላ ሰነድ አልባ ስደተኞች እስ ሰኔ 23/ 2018 ዓ.ም. (በጎርጎሮሳዊያኑ እስከ ሰኔ 30) ድረስ አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ ወስነዋል።
በእጃቸው ዱላ የያዙት ተቃዋሚዎቹ "መሄድ አለባቸው" እያሉ በአገሬው ዙሉ ቋንቋ ሲዘምሩ ሰንብተዋል።
የተቆረጠው ቀን ሲቃረብ ማክሰኞ ዕለት ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ለአገሪቱ ውስብስብ የምጣኔ ሀብት ችግር "የተጋለጡትን ሰዎች የጦስ ዶሮ" እያደረጉ ያሉ ደቡብ አፍሪካውያንን አስጠንቅቀዋል።

እስናት ጆሴፍ ከሦስት ዓመት በፊት ወደ ደቡብ አፍሪካ በመምጣት ልጆቿን እስከምትወልድ ድረስ የቤት ሠራተኛ ሆና ትሰራ ነበር።
ሕጋዊ ሁኔታዋ ግልፅ አይደለም። ፓስፖርቷ እንደጠፋባት እና ሌሎች ሰነዶቿም በሌባ እንደተወሰዱ ትናገራለች። የማሊ ቆንስላ ተስፋ የቆረጡ ዜጎቹን ለመመለስ ከለጋሾች ጋር ባዘጋጃቸው አውቶብሶች ለመመለስ ፍላጎት አላት።
ባለፉት ሳምንታት የጋና፣ ሞዛምቢክ፣ ናይጄሪያ እና ዚምባቡዌ መንግሥታት ዜጎቻቸውን በአየር እና በየብስ አስወጥተዋል። እስካሁን 3,500 የሚሆኑ ስደተኞች በፈቃደኝነት ደቡብ አፍሪካን ለቅቀው ወጥተዋል።
የደቡብ አፍሪካ ባለሥልጣናት በሕገ ወጥ መንገድ በአገሪቱ የነበሩ ከ500 በላይ የሚሆኑ ናይጄሪያዊያን መውጣታቸውን ገልፀዋል።
ከዘጠኝ ዓመታት የደቡብ አፍሪካ ቆይታ በኋላ ባለፈው ሳምንት ሌጎስ የደረሰው ቤንጃሚን ለቢቢሲ፤ "ደቡብ አፍሪካውያን የውጭ አገር ሰዎችን አይወዱም፤ በተለይ ናይጄሪያውያንን። ደቡብ አፍሪካ ለመኖር የምታስችል አይደለችም፤ በየትኛውም ጊዜ ሕይወትህን ልታጣባት የምትችል አገር ናት" ብሏል።
የተቃውሞ አዘጋጆች እርምጃቸው የመጤ ጠልነት መሆኑን ያስተባብላሉ። ሌሎች አፍሪካዊያን ስርዓቱን እየበዘበዙ መሆኑ እንደሰለቻቸው ይናገራሉ። 'የማርች ኤንድ ማርች' መሪ ጃሲንታ ነጎብስ-ዙማ "ተጎጂ ነን የሚል ካርድ እየተጫወቱ ነው" ሲሉ ሁኔታውን ይገልፃሉ።
"ወደ ደቡብ አፍሪካ ለ30 ቀናት በሚያስቆይ ፓስፖርት ከመጣችሁ፤ 50 ቀን ሲሆን፣ ሁለት ዓመት ሲሆን፣ አምስት ዓመት ሲሆን ሕጉን እየጣሳችሁ እንደሆነ ማወቅ አለባችሁ" በማለት በደርባን በአንድ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ደቡብ አፍሪካ ለወደቁ አገራት የስደተኞች ጣቢያ እንድትሆን አንፈቅድም። . . .ሁሉም አገር ለራሱ ዜጎች ቅድሚያ ይሰጣል እናም የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ይህን እንዲያደርግ እንፈልጋለን።"
የቅርብ ጊዜ መረጃዎች ደቡብ አፍሪካ የሦስት ሚሊዮን የውጭ አገር ዜጎች መኖሪያ መሆኗን ያሳያሉ። ይህም ከአጠቃላይ የሕዝብ ቁጥሩ አምስት በመቶ ነው።
ነገር ግን መረጃዎቹ በአገሪቱ ሰነድ አልባ የሆኑ ስደተኞች ቁጥርን አያንፀባርቁም ተብሎ ይታመናል። ይህም ለተቃዋሚዎች ዋነኛ የክርክር ምንጭ ነው።
የተቃዋሚዎች ብስጭት በአገሪቱ እያደገ ባለው የሥራ አጥነት ቁጥር እና የምጣኔ ሀብት ኢ-እኩልነት ላይ ያጠነጥናል።
ደቡብ አፍሪካ የዓለማች ከፍተኛው የሥራ አጥ ምጣኔ ያለባት አገር ስትሆን፤ 32.7 በመቶ ሕዝቧ ሥራ አጥ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በ2026 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 350 ሺህ ሥራ አጥነት የተመዘገበ ሲሆን፤ አብዛኞቹም ወጣቶች ናቸው።
ይሁን እንጂ የአህጉሩ ከፍተኛ አዳጊ አገር የሆነችው ደቡብ አፍሪካ ድሃ ከሆኑ አገራት የሚመጡ ዜጎች ጥበቃ እና የቤት ሠራተኛ ሆነው ለመስራት ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው መኖር ይፈልጋሉ።
እንደ መቻ ራሞሮላ ያሉ የተቃውሞ ሰልፈኞች የደቡብ አፍሪካ ሕዝቦች "እጥረት ያለበትን ሀብት ለመጠቀም ይፋለማሉ" በማለት የሕዝብ አገልግሎቶች ላይ ያለውን ጫና ይገልፃሉ።
"ልጆቻችንን ትምህርት ቤት ለማስገባት እየተቸገርን ነው። አዛውንት ሰዎቻችንን ሆስፒታል ለማስገባት እየተቸገርን ነው" በማለት ለቢቢሲ በአገሪቱ ዋና ከተማ ፕሪቶሪያ በተደረገ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ተናግሯል።
ይሁን እንጂ እነዚህ ተቃውሞዎች በ2008፣ 21 ደቡብ አፍሪካዊያንን ጨምሮ 62 ሰዎች እንደተገደሉበት ዓይነት ብጥብጥ ሊያመሩ ይችላል የሚል ስጋት አለ። ይህ ነውጥ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤታቸው በኃይል ለቀው እንዲወጡ አድርጓል። በ2015፣ 2016 እና 2019 የመጤ ጥላቻ አመፆችም ተቀስቅሰው ነበር።
ባለፈው ወር የሞዛምቢክ መንግሥት በምዕራብ ኬፕ ግዛት አምስት ዜጎቹ በመጤ ጥላቻ ጥቃቶች መገደላቸውን አስታውቋል። የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህን ውድቅ አድርጎ፤ ሁለት ሞዛምቢካውያን መገደላቸውን እና የግድያቸው ሁኔታ እየተመረመረ ነው ብሏል።
በማኅበራዊ የትስስር ገፆች የሚለቀቁ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች በውጭ አገር ዜጎች ላይ ጥቃቱን እያነሳሱ ነው።
በአንድ ምሥል ላይ የጋና ዜጋ ወደ አገሩ እንዲመለስ በተቃዋሚዎች ዛቻ ሲደርስበት ይታያል። ይህም ጋና የደቡብ አፍሪካ አምባሳደርን ጠርታ ለውጭ አገር ዜጎች ጥበቃ እንዲደረግ እንድትጠይቅ አስገድዷል።
ሌላ በስፋት በተሰራጨ ተንቀሳቃሽ ምሥል በፌስቡክ 1.4 ሚሊዮን ተከታዮች ካሉት ነኮሲከሆና ነዳባነዳባ የተባለ ታዋቂ ተቃዋሚ መንገድ ዳር አንድን ወንድ በመጠጋት ዜግነቱን ሲጠይቀው ታይቷል።
የኮንጎ ዜጋ እንደሆነ ሲነግረው ነዳባነዳባ የዙሉ ባህላዊ ልብሱን ለብሶ የሕጋዊነት ሁኔታውን ሳይጠይቅ እንዲህ ብሎታል፤ "ሰኔ 23 የመጨረሻው ቀን ነው። ነገር ግን ይህ ማለት ሰኔ 23 ለቅቀህ መውጣት አለብህ ማለት አይደለም። አሁኑኑ ውጣ።"

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
በሕጋዊ መንገድ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ የውጭ አገር ዜጎችም ዒላማ እንደሆኑ ይናገራሉ። አንዳንዶች በደርባን የአገር ውስጥ ጉዳይ ቢሮ አቅራቢያ ለጥበቃ በሚል ተጠልለዋል።
የብሩንዲ ዜጋ የሆነች አንዲት ሴት "በደቡብ አፍሪካ የስደተኝነት ሁኔታዬን እውቅና የሚሰጥ ሰነድ አለኝ። ነገር ግን ሁላችንም እየባረርን ነው" በማለት ከአራት ልጆቿ ጋር በተጠለለችበት ለቢቢሲ ተናግራለች።
"ለሕይወቴ በጣም ፈርቻለሁ። ልጆቹ ፈርተዋል። ምንም ክብር የለም። እዚህ ስታልፍ ትሰደባለህ። ልጆቹ ትምህርት ቤት እንኳ ይሰደባሉ" ትላለች ከክረምቱ ቅዝቃዜ ራሷን ለመጠበቅ በብርድ ልብሷ እየተሸፋፈነች።
በኬፕ ታውን የውበት ባለሙያ የሆነችው ማላዊ በደቡብ አፍሪካ ለ16 ዓመት ያለ ሰነድ ኖራለች። ለቢቢሲ በዚህ ጊዜ ወደ ሱቅ መሄድ እንኳ ዛቻ ያስከትላል ትላለች።
ባለቤቷ እና እርሷ ከዘጠኝ ዓመት ልጃቸው ጋር ከግብይት ማዕከል ሲመለሱ ታክሲ ውስጥ አስፈሪ ክስተት ገጥሟቸዋል። "ኡበር [ሜትር ታክሲ] ውስጥ ነበርን፤ ሦስታችንም። በታክሲ ሹፌሩ ሰነዳችንን ተጠየቅን። 'ከየት ነው የመጣችሁት? አወራራችሁ ለየት ይላል' አለን።"
የውበት ባለሙያዋ ፕሬዝዳንት ራማፎሳ ሕገ ወጥ ስደትን ለመቆጣጠር የትግበራ ዕቅድ ማውጣታቸውን እንደምትረዳ ገልፃ፤ ነገር ግን የሰው ልጆች ሕጋዊ ይሁኑ አይሁኑም የደኅንነት መብት እንዳላቸው አጽንኦት ሰትታ ታስረዳለች።
"ልጄ ትምህርት ቤት እንኳ አትሄድም። ምክንያቱም አሁን ምን እንደሚከሰት ፈርተናል።"
ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ለሕዝብ ባሰራጩት ንግግራቸው የትኛውም ግለሰብ ሆነ ቡድን ሰዎችን የዜግነት ማስረጃ እንዲያቀርቡ መጠየቅ እንደሌለበት ያስጠነቀቁ ሲሆን፤ መንግሥታቸው እርምጃ እንደሚወስድ ተናግረዋል።
"ደኅንነት" ካለባቸው አገራት በኩል የሚመጡ ስደተኞችን የጥገኝነት ጥያቄን ውድቅ የሚያደርግ እና አገሪቱ ዜግነት የምትሰጣቸውን እና ዜጎቿ ላልሆኑ ስተኞች የመታወቂያ አዲስ ኮታን ያካተት እርምጃ እና ቀውሱን ለመቆጣጠር ያለመ ባለ አምስት ነጥብ ዕቅድ ይፋ አድርገዋል።
በአዲሰ እርምጃ ሰነድ አልባ የሆኑ ስደተኞች በአነስተኛ ክፍያ የሚቀጥሩ አሰሪዎች እስራት ይጠብቃቸዋል።
ራማፎሳ ጥረታቸው ስርዓቱን የሚበዘብዙ ሙሰኞች ላይ እርምጃ መውሰድን እንደሚያካትትም ተናግረዋል።

ተቃውሞች የተበራከቱት በመጪው ኅዳር የፖለቲካ ፓርቲዎች ለማሸነፍ ድጋፍ እያሰባሰቡ ባለበት ወቅት ነው።
ፖለቲከኞች በሕገ ወጥ ስደት ዙሪያ ፍርሃት እና ንዴትን ለመቀስቀስ ሐሰተኛ መረጃዎችን ይጠቀማሉ።
የደቡብ አፍሪካ መንግሥት እስካሁን 40 ሺህ ሕገ ወጥ ስደተኞችን የኢምግሬሽን ሕጉን በመጣስ በቁጥጥር ስር እንዳዋለ በዚህ ሳምንት አስታውቋል።
"ኦፕሬሽን ኒው ብሩም" በሚል የሚታወቀው እርምጃው በጆሀንስበርግ በመንገድ ዳር በኢ-መደበኛ የተገነቡ ሱቆችን ሲያፈርስ ታይቷል።
የአገሬው ባለሥልጣናት አካባቢዎቹ ለወንጀል እና ሕገ ወጥ ስደተኞች "ዋነኛ መገኛ" ናቸው ይላሉ።
የቢቢሲ ጋዜጠኛ በአካባቢው ጉብኝት ባደረገበት ቀን ኢትዮጵያዊ ስደተኞች ፍርስራሹን በሀዘን እየተመለከቱ ነበር። ስደተኞቹ በባለሥልጣናት ማስጠነቀቂያ ተሰጥቷቸው ነበር።
እንደዚህ ዓይነት እርምጃዎች እና ተቃውሞች ስደተኞች አማራጭ እንደሌላቸው እንዲሰማቸው እያደረገ ነው።
"ሰኔ 23 ደቡብ አፍሪካውያንን ልቆጣጠር አልችልም" ይላል ዋነኛ ተቃዋሚ የሆነው ነኮሲከሆና ነዳባነዳባ።
ለመውጣት በብርቱ የፈለጉ የውጭ አገር ዜጎች የሞዛምቢክ ድንበር በተሽከርካሪዎች ሰልፍ መሙላታቸው እየተነገረ ነው።
በደርባን ሜዳ የተጠለሉ በአብዛኛው ሰነድ አልባ የማሊ ዜጎች ደቡብ አፍሪካን ለቅቀው እስኪወጡ ድረስ ቸኩለዋል።
ባለፈው እሑድ የመጀመሪያው አውቶብስ ተመላሾችን ይዞ ሲወጣ በዙሉ ቋንቋ "እየሄድን ነው" በማለት እየዘመሩ ነበር።















