በርካታ ተጫዋቾች በኮቪድና በጉዳት ያላሰለፉት ሌስተሮች ሊቨርፑልን አሸነፉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ትናንት ማክሰኞ ምሽት በሊቨርፑልና ሌስተር ሲቲ መካከል የተደረገው ተጠባቂ ጨዋታ አዴማላ ሉክማን ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ በሌስተር አሸናፊነት ተጠናቋል። በዚህም ሊቨርፑሎች በደረጃ ሰንጠረዡ ከማንቸስተር ሲቲ በስድስት ነጥብ ርቀው ሁለተኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ ተገደዋል።
ሊቨርፑሎች በመጀመሪያው አጋማሽ 15ኛው ደቂቃ ላይ የፍጹም ቅጣት ምት አግኝተው የነበረ ቢሆንም ግብፃዊው ሞሐመድ ሳላህ ወደ ግብነት መቀየር ሳይችል ቀርቷል። የጨዋታው ኮከብ ተጨዋች ተብሎ የተመረጠው የሌስተሩ ግብ ጠባቂ ካስፐር ሹማይክል ኳሷን ከመረብ እንዳትገናኝ አድርጓል።
ሴኔጋላዊው ሳዲዮ ማኔም ቢሆን በርካታ የግብ ዕድሎችን ቢያገኝም ግብ ማስቆጠር ግን አልቻለም። አብዛኛውን የጨዋታ ጊዜ ወደ ግብ ክልላቸው ተስበው ለመከላከል ተገድደው የነበሩት ሌስተሮች 59ኛው ደቂቃ ላይ ያገኙትን ዕድል በአግባቡ ተጠቅመዋል።
የቀድሞው የኤቨርተን የፊት መስመር ተጫዋች አዴማላ ሉክማን ተቀይሮ በገባ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ኪረን ደውስብሪ ያሻማለትን ኳስ ወደ ግብነት መቀየር ችሏል።
በርካታ የመጀመሪያ ቡድን ተጫዋቾችን በጉዳትና በኮቪድ ምክንያት ያጡት ሌስተሮች በተደጋጋሚ ሊቨርፑሎች ሲያደርጉት የነበረው የማጥቃት ጨዋታ ተቋቁመው አምሽተዋል።
ከስድስት ቀናት በፊት በካራባዎ ዋንጫ ሁለቱ ቡድኖች ተገናኝተው የነበረ ሲሆን ሌስተር ሲቲ ቀድሞ 3 ለ 0 መምራት ችሎ ነበር። ነገር ግን በተከታታይ ባስተናገዱት ሦስት ግብ ምክንያት ጨዋታው አቻ ተጠናቆ በፍጹም ቅጣት ምት ሊቨርፑል ማሸነፍ ችሏል።
ፕሪምየር ሊጉ ከተጀመረ ሁለተኛ ሽንፈታቸውን ያስተናገዱት ሊቨርፑሎች ከሊጉ መሪ ማንቸስተር ሲቲ በስድስት ነጥብ ርቀው በ41 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። በሌላ በኩል ከሰባት ጨዋታዎች ሁለቱን ብቻ ማሸነፍ የቻሉት ሌስተሮች ትናንት ምሽት ሦስት ሙሉ ነጥብ ማግኘታቸውን ተከትሎ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችለዋል።
በጉዳት ምከንያት ተከላካዮቻቸውን ያጡት ሌስተሮች የመሀል ክፍል ተጫዋቹ ዊልፍሬድ ንዲዲን በተከላካይ መስመር ለማሰለፍ ተገድደው ነበር። ንዲዲም ሞሐመድ ሳላህ ላይ በፈጸመው ጥፋት ቡድኑ ላይ የፍጹም ቅጣት ምት አስሰጥቶ የነበረ ቢሆንም ግብ ጠባቂው ግን ኳሷ ግብ እንዳትሆን አድርጓል።
የሌስተሩ አጥቂ ጄሚ ቫርዲ ምሽቱን ሙሉ ያገኘውን ኳስ ወደ ሊቨርፑል ግብ ክልል ይዞ በመግባት ትልቅ ፈተና ሆኖ አምሽቷል። በመጀመሪያው አጋማሽም ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ ቢመታም ተከላካዩ ጆዌል ማቲፕ ተደርቦ ግብ ከመሆን አድኖበታል።
ሊቨርፑሎች ከሜዳቸው ውጪ ካደረጓቸው 29 ጨዋታዎች በትናንቱ ጨዋታ ላይ ብቻ ነው ግብ ማስቆጠር ያልቻሉት። የፊታችን እሁድ ከቼልሲ ጋር የሚፋለሙት ሊቨርፑሎች በደረጃ ሰንጠረዡ ከማንቸስተር ሲቲ ያላቸውን ልዩነት ለማጥበብ የሞት የሽረት ትግል እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በአፍሪካ ዋንጫ የሚሳተፉት የሊቨርፑሎቹ ሞሐመድ ሳላህ፣ ሳዲዮ ማኔ እና ናቢ ኬታ ወደ ውድድሩ ከመሄዳቸው በፊት የቼልሲው ጨዋታ የመጨረሻቸው ይሆናል።
ትናንት በተካሄዱ ሌሎች የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች በጥሩ አቋም ላይ የሚገኙት ቶተንሀሞች ከሳውዝሀምፕተን ጋር አንድ አቻ ሲለያዩ ዌስት ሀም ደግሞ ዋትፎርድን 4 ለ1 በማሸነፍ ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል መመለስ ችለዋል።
በቀድሞው አርሰናል ተጫዋች ፓትሪክ ቪዬራ የሚመሩት ክሪስታል ፓላሶች ደግሞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኙት ኖርዊቾችን ሶስት ለባዶ አሸንፈዋል።
ሰኞ ምሽት የተደረገው የማንቸስተር ዩናይርድና የኒውካስል ጨዋታ አንድ አቻ መጠናቀቁ የሚታወስ ነው። ዛሬ ምሽት ደግሞ ቼልሲ ከብራይተን እንዲሁም የሊጉ መሪ ማንቸስተር ሲቲተ ከብሬንትፎር የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።














