ዘጠኝ ግብ በተስተናገደበት ጨዋታ ማንቸስተር ሲቲ ድል ተቀዳጅቷል

ራሂም ስተርሊንግ በፍፁም ቅጣት ምት ያስቆጠራር ግብ

የፎቶው ባለመብት, PA Media

የምስሉ መግለጫ, ራሂም ስተርሊንግ በፍፁም ቅጣት ምት ያስቆጠራር ግብ
ታትሟል

በፈረንጆቹ የገና በዓል ማግስት ማንቸስተር ሲቲዎች ለዘጠነኛ ተከታታይ ጊዜ በማሸነፍ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ደረጃ ሰንጠረዥን በስድስት ነጥብ ልዩነት መምራት ጀምረዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ እሁድ ዕለት ከሌስተር ሲቲ ጋር የተገናኙነት ሲቲዎች ጨዋታው በተጀመረ በአምስተኛው ደቂቃ ነበር ግብ ማስቆጠር የቻሉት።

ጨዋታው 25ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ማንቸስተር ሲቲዎች ሌስተርን 4 ለ 0 እየመሩ ነበር። በድንቅ አቋም ላይ የሚገኙት ሲቲዎች ምንም እንኳን ጨዋታውን 6 ለ 3 በሆነ ውጤት ቢያሸንፉም ከእረፍት መልስ ሌስተሮች በእጅጉ ተሽለው አጥቅተው መጫወት ችለዋል።

በሚያስገርም መልኩም ሌስተሮች በአስር ደቂቃዎች ውስጥ 3 ግቦችን በማስቆጠር ትልቅ መነሳሳትን መፍጠር ቢችሉም፣ በኮቪድ ወረርሽኝ እንዲሁም በጉዳት ክፉኛ እየተፈተነ የሚገኘው የተከላካይ መሰመራቸው ተጨማሪ ሁለት ግቦችን በማስተናገዱ ከሽንፈት ማምለጥ ሳይችሉ ቀርተዋል።

ከማንቸስተር ሲቲ በመቀጠል ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ሊቨርፑሎች ከሊድስ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለሌላ ጊዜ የተላለፈ ሲሆን በዚህም ምክንያት ሲቲዎች የደረጃ ሰንጠረዡን በስድስት ነጥብ ልዩነት መምራት ችለዋል።

ስድስት ግቦችን ያስተናገዱት ሌስተሮች በርካታ ተጫዋቾቻቸውን በጉዳትና በኮቪድ ምክንያት ቢያጡም በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ሲቲዎችን ባልተለመደ መልኩ ሲፈትኗቸው ተስተውሏል።

ከጨዋታው ቀደም ብሎ የሲቲተው አሰልጣኝ ፔፕ ጉዋርዲዮላ እንደ ቡድን ኳስ ይዘን መጫወታችን ይጠቅመናል እንጂ በግል ተጫዋቾቼን ከተመለከታችኋቸው መከላከል ላይ እስከዚህም ናቸው ሲል ተደምጦ ነበር።

ከሌስተር በነበራቸው ጨዋታም የተስተዋለው ይሄው ነው። በሁለተኛው አጋማሽ በአስር ደቂቃዎች ውስጥ ያስተናገዷቸው ሦስት ግቦች ባለፉት ሳምንት ጨዋታዎች ካስተናገዷቸው ግቦች ጋር እኩል ነው። ሌስተሮች ተጨማሪ ግቦችን ማስቆጠር የሚችሉበትን ዕድል ቢፈጥሩም ወደ ግብ ግን መቀየር ሳይችሉ ቀርተዋል።

በሌሎች 'የቦክሲንግ ደይ' ጨዋታዎች አርሰናል ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኙት ኖርዊች ሲቲዎችን አምስት ለባዶ በሆነ ሰፊ ውጤትአሸንፈዋል።

በድንቅ አቋም ላይ የሚገኘው ቡካዮ ሳካ ለአርሰናል የመጀመሪያዋን እና ሦስተኛዋን ግብ በማስቆጠር በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘው የፈንጆቹን ዓመት በግብ ታጅቦ ማጠናቀቅ ችሏል።

ይህንን ተከትሎም አርሰናል በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ከበርካታ ዓመታት በኋላ በደረጃ ሰንጠረዡ በ35 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።

አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቶተንሀም ደግሞ ትናንት ምሽት ከክሪስታል ፓላስ ያደረገውን ጨዋታ ሦስት ለባዶ በሆነ ውጤት አሸንፏል። በዚህ ጨዋታ ወደ አቋሙ ለመመለስ ተቸግሮ የቆየው ሃሪ ኬን ግብ ማስቆጠር ችሏል።

በዘንድሮው የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ በርካቶችን ማስገረም የቻሉት ዌስት ሀሞች በሳውዝሀምፕተን ሦስት ለሁለት ተሸንፈዋል። በዴቪድ ሞዬስ ሚመሩት ዌስትሀሞች ባለፈው ዓመት በቻምፒየንስ ሊግ ለመሳተፍ ከፍተኛ ትንቅንቅ ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም ነበር።

ዘንድሮ ግን ድንቅ አቋም በማሳየት ቢቀጥሉም ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ያስተናገዷቸው ሽንፈቶች ዋጋ አስከፍሏቸዋል። አሁን ላይ ዌስትሀም በ28 ነጥብ ስድተኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኙት።

ቼልሲ ደግሞ ትናንት ምሽት አስቶን ቪላን ሦስት ለአንድ በሆነ ውጤት በማሸነፍ በፕሪምየር ሊጉ የሦስተኝነት ቦታቸውን ማስጠበቅችለዋል። ዛሬ ሰኞ ምሽት አምስት ሰዓት ላይ ደግሞ ማንቸስተር ዩናይትድ ከኒውካስል የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።