ሆስፒታል ውስጥ ህሙማንን ሆነ ብሎ ገድሏል የተባለው አሜሪካዊ ነርስ ጥፋተኛ ተባለ

መርፌ የያዘ ነርስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በአሜሪካ ቴክሳስ ግዛት ውስጥ አራት ህሙማንን ሆን ብሎ ገድሏል ተብሎ የተከሰሰው ነርስ በከባድ የግድያ ወንጀል ጥፋተኛ ተባለ።

የ37 ዓመቱ ነርስ ዊሊያም ዴቪስ የልብ ህክምና የተደረገላቸውን አራት ታካሚዎችን በተለያዩ ጊዜያት ከቀዶ ህክምና በኋላ በደም ስራቸው በኩል አየር በመርፌ በመውጋት ለሞት አብቅቷቸዋል ተብሎ ነው የተከሰሰው።

ዐቃቤ ሕግ እንደ አውሮፓውያኑ ከ2017 አስከ 2018 ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ነርሱ ሰባት ሰዎች ላይ ይህንኑ ለሞት የሚያበቃ ድርጊት ለመፈጸም ሞክሯል ሲል ከሶታል።

በአራት ህሙማን ሞት ጥፋተኛ የተባለው ነርስ ዊሊያም ዴቪስ የሞት ቅጣት ሊበየንበት እንደሚችል እየተነገረ ነው።

ሲሰራበት የነበረውና ህሙማኑ የሞቱበት ሆስፒታል ከፍርድ ቤቱ ውሳኔ በኋላ እንዳለው "ፍርዱ በድርጊቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ቤተሰቦች ለሐዘናቸው መቋጫ ይሰጣል" ብሎ ተስፋ እንደሚያደርግ ገልጿል።

በነርሱ ግድያው ተፈጽሞባቸዋል የተባሉት ከ47 አስከ 74 ዓመት እድሜ የሚደርሱ ወንዶች ሲሆኑ፣ ግለሰቦቹ ቀዶ ህክምና ካደረጉ በኋላ በደም ስራቸው በኩል አየር በመርፌ ተወግተው በአንጎላቸው ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱ ተነግሯል።

ለፍርድ ቤት የቀረበው ማስረጃ እንዳመለከው በነርሱ የተገደሉት አራቱ ሰዎች ከቀዶ ህክምናው በኋላ በጥሩ ሁኔታ እያገገሙ የነበሩ በመሆናቸው ችግሩ ሲከሰት ዶክተሮች በጣሙን ግራ ተጋብተው ነበር ተብሏል።

ባለሥልጣናት እንዳሉት በህሙማኑ ላይ በተደረገ የሲቲ ስካን ምርመራ ላይ ዶክተሮች አየር በአንጎላቸው ውስጥ በተመለከቱበት ወቅት ነው አንዳች ችግር ሊኖር እንደሚችል ጥርጣሬ የተፈጠረባቸው።

ታዋቂው ዶክተር ዊሊያም ያርብሮ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት ለአስርት ዓመታት በቆዩበት የህክምና ሙያ ውስጥ እንዲህ ያለ ችግር በህሙማን ላይ ፈጽሞ እንዳላጋጠማቸው ገልጸዋል።

በፍርድ ሂደቱ ወቅት በታየው በሆስፒታሉ የደኅንነት ካሜራ የተቀረጸ ምሰል ላይ ነርሱ ወደ አንደኛው ህመምተኛ ክፍል ውስጥ ሲገባ ታይቷል።

ከዚያ ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ የልብ መቆጣጠሪያ መሳሪያው የማስጠንቀቂያ ድምጽ ያሰማ ሲሆን ቆይቶም ህመምተኛው በተወጋው መርፌ ምክንያት ህይወቱ አልፏል።

የነርሱ ጠበቃ ግን ህመምተኞቹ በተፈጸመባቸው ድርጊት ህይወታቸው ማለፉን የሚያመለክት ማስረጃ የለም በማለት ነርሱ ዴቪስ ሆስፒታሉ ላጋጠመው ከባድ የአሰራር ችግር መሸፈኛ ሰበብ ተደርጓል በማለት በፍርድ ቤቱ ተከራክሯል።

ፍርድ ቤቱ በነርሱ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ካሳለፈ በኋላ ዐቃቤ ሕግ "ሰዎችን በመግደል ይደሰታል" ያለው ዴቪስ በሞት እንዲቀጣ ይጠይቃል ተብሏል።