ሞባይል የሰረቀው ግብፃዊ በቀጥታ ባሰራጨው ቪዲዮ አማካኝነት ተያዘ

የፎቶው ባለመብት, Youm7/Facebook
ግብፅ ውስጥ በሞባይል ስልኩ በቀጥታ የቪዲዮ ዘገባ ሲያስተላልፍ ከነበረ ጋዜጠኛ ላይ ስልኩን ነጥቆ ያመለጠ ሌባ የፊቱ ገጽታ ከታየ በኋላ በቁጥጥር ስር ዋለ።
ንጥቂያው የተከሰተው ማህሙድ ራጊብ የተባለ ዩም7 ለተባለ የዜና ድረ ገጽ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲመለከቱት የነበረን የቀጥታ ዘገባ ሲያቀርብ ነበር።
ሌባው በሞተር ሳይክል እየተጓዘ የጋዜጠኛውን ስልክ ከእጁ ላይ ነጥቆት ካመለጠ በኋላ የቀጥታ ስርጭቱ አልተቋረጠም ነበር። ከዚያም ሌባው እጁ የገባው ስልክ እያገላበጠ ሲመለከት የሌባው ገጽታ በግልጽ መታየት ችሎ ነበር።
ሞተር ሳይክሉ ላይ ተቀምጦ እየተጓዘ ከነሲጋራው የታየውን ሌባ ፖሊስ ወዲያውኑ ነበር በቁጥጥር ስር ለማዋል የቻለው።
ጋዜጠኛው በግብፅ አራተኛ ትልቅ ከተማ በሆነችው ሱብራ አል-ኻይማህ የደረሰውን የመሬት መንቅጥቀጥን ተከትሎ ስላለው ሁኔታ ከአንድ ድልድይ ላይ ሆኖ የቀጥታ ዘገባ እያስተላለፈ ነበር።
ሪፖርተሩ ድልድዩ ያለበትን ሁኔታ በቀጥታ እየቀረጸ ሲያሳይ ነበር ባለሞተር ሳይክሉ ሌባ ሞባይል ስልኩን ከእጁ ላይ የሞጨለፈው።
ሌባው ከአካባቢው ጥቂት ራቅ ብሎ አፉ ላይ ሲጋራውን እንደለጎመ የነጠቀውን ስልክ ሲመለከት እንዲሁም የተከተለው ሰው እንዳለ ወደ ኋላው ሲያይ የሚያሳይ የቪዲዮ ምስል በቀጥታ ታይቷል። በዚህም ሳቢያ ግለሰቡ በበርካታ ግብፃውያን ዘንድ መነጋገሪያ ሆኗል።
ይህን ክስተት በቀጥታ ሲተላለፍ ከ20,000 በላይ ሰዎች እንደተመለከቱት የፌስቡክ መረጃ ሲያመለክት፣ ከዚያ በኋላም ከ24 ሰዓታት ጥቂት አለፍ ባለ ጊዜ ውስጥ ከ6.2 ሚሊዮን በላይ ተመልካች አግኝቷል። በተጨማሪም 45,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ አስተያየት ሰጥተዋል።
በሰረቀው ስልክ አማካኝነት በዚህ ሁሉ ሰው ፊቱ የታየው ቀማኛ በሕግ አስከባሪዎች እጅ ላይ በቀላሉ እንዲወድቅ አድርጎታል።
የግብፅ የአገር ውስጥ ሚኒስቴር ሌባው በቁጥጥር ስር መዋሉን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ላይ ግለሰቡ "ሥራ የሌለው" እንደሆነና የነጠቀውን ሞባይልም እንደሸጠው አመልክቷል።
















