ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሶሪያ እርስ በርስ ጦርነት ከ350 ሺህ በላይ ሰዎች ተገድለዋል- ተመድ
በሶሪያ ውስጥ በ10 ዓመታት እርስ በርስ ጦርነት ቢያንስ 350 ሺህ209 ሰዎች መገደላቸውን የተባበሩት መንግስታት ከአውሮፓውያኑ 2014 ወዲህ ባደረገው የመጀመሪያ ይፋዊ የሞት ቁጥር አስታውቋል።
ሆኖም የተመድ የሰብዓዊ መብት ኃላፊ አኃዙ ድርጀቱ ማንነታቸው የለያቸው ሰዎች እንጂ በጦርነቱ የተገደሉ ሰዎችን ቁጥር በትክክል አያሳይም በማለት አስጠንቅቀዋል።
በዩናይትድ ኪንግደም ተቀማጭ የሆነ ይህንን የሚመራ ተቆጣጣሪ ቡድን በኩሉ የሟቾችን ቁጥር ከ600 ሺህ በላይ አድርሶታል።
በሶሪያ ውስጥ ያለው ጦርነት በአሁኑ ወቅት በጂሃዲስቶችና አማፅያን ቁጥጥር ስር ባለ አንድ ግዛት ብቻ ተወስኗል።
የጦርነቱ ከፍታ ደርሶበታል በሚባለው በአውሮፓውያኑ 2015 ታጣቂ ቡድኖች የአገሪቱን ሰፊ ግዛቶች ተቆጣጥረው የነበረ ቢሆንም ሩሲያ ፕሬዚዳንት በሽር አል አሳድን ደግፋ በጦርነቱ ጣልቃ መግባቷ የጦርነቱን ሂደት ቀይሮታል።
ውጊያው የተጀመረው በአውሮፓውያኑ 2011 ሲሆን መነሻውም ፕሬዚዳንት አሳድ አምባገናነዊ አገዛዝን የተቃወሙ ሰልፈኞች ላይ የፀጥታ ኃይሎች ተኩስ መክፈታቸውን ተከትሎ ተቃዋሚዎቹ ወደ ትጥቅ ትግል መግባታቸው ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ከአውሮፓውያኑ 2014 በኋላ የሟቾችን ቁጥር መመዝገብ በይፋ አቁሞ ነበር።
ምክንያቱም ተመድ መረጃው የተመሰረተው በሶሪያ ውስጥ ይንቀሳቀሱ የነበሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የነበሩ ሲሆን ከጦርነቱ መፋፋም ጋር ተያያዞም የድርጅቶቹ ቁጥር ተመናምኗል።
በዚህም የተነሳ መሬት ላይ ያለውን የሟቾቹን ቁጥር በትክክለኛው የሚያሳይ መረጃም ለማግኘት ተቸግሮ ነበር።
ነገር ግን ጦርነቱ በዚህ አመት አስረኛ አመቱን ማስቆጠሩን ተከትሎ የተባበበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ለሰብዓዊ መብቶች ፅህፈት ቤት በአገሪቱ ውስጥ ምን ያህል ሰዎች እንደተገደሉ ለማወቅ እንዲሞክር ተጠይቋል።
በያዝነው ሳምንት አርብ ለምክር ቤቱ ሪፖርት ያደረጉት የተመድ የሰብዓዊ መብት ኃላፊ ሚሸል ባችሌት "ውስብስብ እና አድካሚ ስራ" ያሉት ሲሆን ተለይተው የታወቁ ሟቾች ቁጥር 350 ሺህ 209 ነው ብለዋል።
ሟቾቹ የሲቪል እና ተዋጊዎችን ቁጥር ያካተተ ሲሆን፣ ጊዜውም ባለፉት አስር አመታት ከአውሮፓውያኑ 2011 እስከ 2021 ነው።
የሰብዓዊ መብት ኃላፊዋ እንዳሉት ከነዚህም ውስጥ የሴቶች ሟቾች አኃዝ እንደ ህፃናቱ ሁሉ ስምንት በመቶ ገደማ ነው።
"ከእያንዳንዱ ከተመዘገበው ሞት በስተጀርባ በነፃነት፣ በእኩልነት በክብር እና በመብት የተወለደና እና ይሄንን ሊያጣጥም የሚገባ ሰው ነበር" ብለዋል።
አክለውም " ሁልጊዜም ቢሆን የጦርነቱ ሰለባ የሆኑ ሰዎችን ታሪክ እንደ ግለሰብም ቢሆን እንደ ማህበረሰብ በደማቁ ልንናገር ይገባል ምክንያቱ እንደነዚህ አይነት ኢ-ፍትሃዊነት እና አሰቃቂ ሁኔታዎች እርምጃ እንድንወስድ ስለሚያስገድደን" በማለትም አስረድተዋል።
ሆኖም በአሁኑ ወቅት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ይዞት የወጣው አኃዝ "በጦርነቱ የተቀጠፉ ሰዎችን ሙሉ ቁጥር አያሳይም። በአሁኑ ወቅት የወጣው አኃዝ መረጋገጥ የቻሉትን ነው" ያሉ ሲሆን ይህም ከተከሰተው አንፃር አናሳ ሊሆን ይችላል ብለዋል።
ከፊል መረጃ ብቻ የያዙ የግድያ ሪፖርቶች በዚህ አኃዝ አልተካተቱም። እንዲሁም ያልተመዘገቡ ግድያዎችና ደብዛቸው የጠፉና የተገደሉ ሰዎችም በተመድ ሪፖርት አልተካተቱም።
የቢቢሲ ዘጋቢ ቢታኒ ቤል ትክክለኛውን የሞት መጠን ማወቅ የተወሳሰበ እና ከባድ ሥራ ነው ብትልም የተባበሩት መንግስታት ባለሥልጣናት በበኩላቸው በጦርነቱ ተጠያቂነትን ለማስፈን ወሳኝነቱን እንደሚናገሩ ታስረዳለች።
በተጨማሪም በህይወት ይኑሩ ይሙቱ ለማይታወቁና በጭንቅና በህመም ላይ ላሉ በርካታ ቤተሰቦችም በተወሰነ መልኩ ጥረቶች እየተደረጉ ነው ለሚለው ማሳያ ነው ተብሏል።
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የተባበሩት መንግሥታት መርማሪዎች በጦርነቱ ወቅት በዘፈቀደ ታስረው የነበሩና በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሲቪሎች ደበዛቸው ጠፍቷል ተብሏል።
በሺዎች የሚቆጠሩ በቁጥጥር ስር ባሉበት ወቅት እንግልትና ስቃይ ደርሶባቸዋል እንዲሁም ተገድለዋል ይህም የጦር ወንጀሎች እና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች መሆናቸውም ተገልጿል።