በጎርፍ የተጥለቀለቁ የለንደን ሆስፒታሎች ታካሚዎችን 'አትምጡ' አሉ

ኒውሀም የተባለው ሆስፒታል ደግሞ ታካሚዎች ወደ ሌሎች የድንገተኛ ክፍሎች እንዲሄዱ ጠይቋል
የምስሉ መግለጫ, ኒውሀም የተባለው ሆስፒታል ታካሚዎች ወደ ሌሎች የድንገተኛ ክፍሎች እንዲሄዱ ጠይቋል
ታትሟል

ሁለት በምሥራቅ ለንደን የሚገኙ ሆስፒታሎች ድንገተኛ ክፍሎቻቸው በጎርፍ በመጥለቅለቃቸው ሳቢያ ታካሚዎች ወደ ሆስፒታሎቹ እንዳይሄዱ አስጠነቀቁ።

ሁለቱ ሆስፒታሎች የጎርፍ አደጋ የደረሰባቸው ትላንት ነው። ዊፐርስ ክሮስ የተባለው ሆስፒታል የኤሌክትሪክ አቅርቦቱ ተቋርጧል። 100 ተኝተው የሚታከሙ ሰዎችን ከሆስፒታሉ ለማስወጣትም ተገዷል።

ኒውሀም የተባለው ሆስፒታል ደግሞ ታካሚዎች ወደ ሌሎች የድንገተኛ ክፍሎች እንዲሄዱ ጠይቋል።

የለንደን እሳት አደጋ መከላከያ ብርጌድ እንዳለው፤ ከ1,000 በላይ ከጎርፍ አደጋ ጋር የተያያዙ የስልክ ጥሪዎች ደርሰውታል።

መኪና ውስጥ ሳሉ የጎርፍ አደጋው የገጠማቸውን ጨምሮ በመኖሪያ ቤታቸው ሆነው ከአደጋው ማምለጥ የተሳናቸው ሰዎችንም መታደግ ተችሏል።

ሁለቱን ሆስፒታሎች የሚያስተዳድረው ማኅበር ቃል አቀባይ "ታካሚዎች ከኛ ሆስፒታሎች ውጪ ያሉ የሕክምና መስጫ አማራጮችን እንዲጠቀሙ እንጠይቃለን" ብለዋል።

ለንደን ውስጥ የሚገኙ አውራ ጎዳናዎች በጎርፍ አደጋው ምክንያት ተዘግተዋል።

ሴንት ፓርክ የተባለው ፓርክ ውስጥ የዝናቡ መጠን 41.6 ሚሊ ሜትር እንደደረሰና፤ ይህም ለንደን ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ በጎርፍ ከተጥለቀሉ ቦታዎች ቀዳሚ እንደሚያደርገው ተገልጿል።

በምሥራቅ ለንደን የሚኖሩ ዜጎች ትላንት ጎርፉ ወደ ቤታቸው እንዳይገባ በመጥረጊያ ወይም የእንጨት ከለላ በመሥራት ሲከላከሉ ነበር።

የሬስቶራንት አስተዳዳሪዋ ማርያ ፔቫ የጎረቤቷ መኝታ ቤት በጎርፍ እንደተዋጠ ተናግራለች። ልጇ ጎረቤቶቿን ከጎርፉ ለመታደግ እየሞከረ እንደነበረም ታክላለች።

"ልጄ ምግብ ሊገዛ ወጥቶ ሲመለስ ሰፈራችን በጎርፍ ተጥለቅልቆ ጠበቀው። ጎርፉ ቤታችን ሊገባም ነበር" ብላለች የ46 ዓመቷ ማርያ።

ሆስፒታሎቹ በመዘጋታቸው አምቡላንሶች ህሙማንን ወደ ሌሎች ሕክምና መስጫዎች ለመውሰድ ተገደዋል።

ኒውሀም የተባለው ሆስፒታል አሁን አገልግሎት እየሰጠ ያለው በእናቶችና ሕፃናት ክፍሉ ነው። ይህ ክፍል በጎርፍ አልተጠቃም።

የሆስፒታሉ ሬዚደንት ክሪስ ዴት "የጎርፍ ውሃው አስፋልቱን አጥለቅልቆት ነበር። መራመድም አይቻልም። ውሃው እስከ ጉልበቴ ድረስ ሞልቶ ስለነበር አውቶብስ ውስጥ ለመግባት ተቸግሬ ነበር" ሲል በትዊተር ገጹ ጽፏል።

የ28 ዓመቱ የለንደን ነዋሪ ኤዲ ኤልየት "እንደዚህ አይነት ነገር ለንደን ውስጥ አይቼ አላውቅም። አውቶብሶች በጎርፍ ተይዘው ቆመው ነበር" ብሏል።

አውቶብሶች በጎርፍ ተይዘው ቆመው ነበር
የምስሉ መግለጫ, አውቶብሶች በጎርፍ ተይዘው ቆመው ነበር