በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ባለ መጥፎ የአየር ፀባይ በርካታ አውሮፕላኖች ለማረፍ መቸገራቸው ተሰማ

የፎቶው ባለመብት, Marina Lystseva
መዳረሻቸውን አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ አድርገው የነበሩ በርካታ አውሮፕላኖች በሌላ አየር ማረፊያዎች እያረፉ መሆኑን ፍላይትራዳር24 አመለከተ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበኩሉ በመጥፎ የአየር ጸባይ ምክንያት ወደ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የሚደረጉ በረራዎች በአቅራቢያ ወደ ሚገኙ አየር ማረፊያዎች ተጉዘው እንዲያርፉ እየተደረጉ ነው ብሏል።
አየር መንገዱ በትዊተር ገጹ ላይ የአገሪቱ ዋነኛና ግዙፍ አየር ማረፊያ በሆነው በቦሌ አየር ማረፊያ እና በዙሪያው ባሉ አካባቢዎች ለአየር በረራ መጥፎ የሚባል የአየር ሁኔታ መኖሩን አመላክቷል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ
"የበረራ ደኅንነት ማረጋገጥ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው" ያለው አየር መንገዱ አውሮፕላኖች በአቅራቢያ በሚገኙ አየር ማረፊያዎች እንዲያርፉ መደረጉ የቅድመ ጥንቃቄው አካል መሆኑን አመልክቷል።
ምንም እንኳ በዚህ መጥፎ አየር ጸባይ ምክንያት የተስተጓጎሉ አውሮፕላኖች ብዛት፣ ከየትኞቹ መነሻዎች የመጡና ወደ የትኛው አየር ማረፊያዎች እያረፉ እንደሆነ ባይገልጽም ፍላይትራዳር24 የተሰኘው ድረ-ገጽ አውሮፕላኖች ወደ የትኞቹ አየር ማረፊያዎች እንዲያርፉ እንደተደረጉ መሆናቸውን አሳይቷል።
እንደ ፍላይትራዳር24 መረጃ ከሆነ ከትናንት እሁድ ጀምሮ እስከ ሰኞ ረፋድ ድረስ ከ35 የማያንሱ መዳረሻቸውን አዲስ አበባ አድርገው የነበሩ በረራዎች ወደ ሌሎች አየር ማረፊያዎች እንዲያመሩ ተደርገዋል።
ከኢትዮጵያ አየር መንገድ በተጨማሪ በዚህ መጥፎ የአየር ጸባይ ምክንያት በረራዎቻቸው ከተስተጓጎሉባቸው አየር መንገዶች መካከል የኳታር እና ቱርክ አየር መንገዶች ይገኙባቸዋል።
መነሻቸውን ከጋምቤላ፣ ኦሶሳና ሰመራ አድርገው የነበሩት በጎንደር አየር አየር ማሪፈያ ሲርፉ፤ ከሰመራ እና ከኬንያዋ የባህር ዳርቻ ከተማ ሞምባሳ የተነሱት አውሮፕላኖች ደግሞ ባሕር ዳር አርፈዋል።
ከኢስታንቡል፣ ዶሃ፣ ካርቱም፣ ዱባይ፣ ጁባ፣ ማፑቶ እና ሌጎስ የተነሱ አውሮፕላኖች ወደ ጂቡቲ ኢንዲያቀኑ ከተደረጉት በረራዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
ከዋሽንግተን፣ ጆሃንስበርግ እና ብራስልስ የተነሱት አውሮፕላኖች ደግሞ ናይሮቢ ኬንያ ያረፉ ሲሆን፤ መነሻቸውን ስቶክሆልም እና ጄኔቫ የነበሩት አውሮፕላኖች ሱዳን ካርቱም አርፈዋል።
ከሪያድ የተነሳው አውሮፕላን አሥመራ ሲያርፍ ከሐርጌሳ የተሳው ደግሞ ድሬዳዋ እንዲያርፍ ሆኗል።
አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የሚያርፉ እና የሚነሱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አውሮፕላኖችን በቀን ያስተናግዳል።
የሱዳን ዜና ወኪል ሱና የአገሪቱ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ኃላፊ የሆኑትን ኢንጂነር ኢብራሂም አደላን ጠቅሶ እንደዘገበው በመጥፎ የአየር ጸባይ ምክንያት በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ማረፍ ያልቻሉ 12 የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላኖች ትናንት ምሽትና ዛሬ ጠዋት ካርቱም እንዳረፉ ገልጿል።
ሱና በዘገባው በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በጭጋጋማ የአየር ሁኔታ ሳቢያ ከ800 ሜትር ርቀት በላይ ማየት የማያስችል የአየር ሁኔታ እንዳለ የጠቀሰ ሲሆን፤ ወደ ካርቱም አየር ማረፊያ ለመጡ አውሮፕላኖች የቴክኒክ እና የሎጂስቲክ ድጋፍ እንደተደረገላቸው የአቪዬሽን ባለስልጣኑ መናገራቸውን አመልክቷል።

እንደ ፍላይትራዳር24 መሠረት ዛሬ ብቻ ከ120 በላይ አውሮፕላኖች በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ያርፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአየር ሁኔታው ሲሻሻል አውሮፕላኖች ወደ ቀደሞ መዳረሻቸው ይመለሳሉ ብሏል በመግለጫው።
አየር መንገዱ ጨምሮም ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ለተፈጠረው ችግር ደንበኞችን ይቅርታ የጠየቀ ሲሆን አየር ጸባይ ሲስተካከልም አሳውቃለሁ ብሏል።












