በቱኒዚያ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ ጠቅላይ ሚንስትሩ ከስልጣናቸው ተነሱ

የቱኒዚያ ተቃዋሚዎች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

በመላው ቱኒዚያ የተቀሰቀሰውን ከፍተኛ አመጽ ተከትሎ ፕሬዝደንቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከስልጣና አንስተው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ደግሞ አገዱ።

በሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች መንግሥት ወረርሽኙን ለመግታት የወሰደውን እርምጃ በመቃወም አደባባይ ወጥተው ቁጣቸውን የገለጹ ሲሆን እሁድ ዕለት ደግሞ ከፖሊስ ጋር መጋጨታቸውም ተገልጿል።

ፕሬዝደንት ካኢስ ሳኤድ በአገሪቱ መረጋጋትን ለመፍጠር እሰራለሁ ካሉ በኋላ አዲስ ጠቅላይ ሚንስትር እንደሚሾሙ ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ ተቃዋሚዎች ፕሬዝደንቱ ጠቅላይ ሚንሰትሩን ማሰናበታቸው እና ምክር ቤቱን ማገዳቸው ከመፈንቅለ መንግሥት ተይቶ አይታይም እያሉ ነው።

"እነዚህን እርምጃዎች የወሰድነው በአገሪቱ ሰላም እስከሚመለስና አገሪቱን ማዳን እንድንችል በማሰብ ነው" ብለዋል ፕሬዝዳንቱ በቴሌቪዥን ባስተላለፉት መልዕክት።

ትናንት ዕሁድ ምሽት ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ሂኬም ሚቺቺ ከኃላፊነታቸው የመነሳት ዜና ከተሰማ በኋላ ዜጎች አደባባይ ወጥተው ደስታቸውን የገለጹ ሲሆን በዋና ከተማዋ ቱኒዝ ደግሞ ፕሬዝዳንቱ ተቃዋሚዎችን ተቀላቅለው ታይተዋል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚ ሰልፈኞች በተለያዩ ከተሞች ዋና ዋና ጎዳናዎች በመሰባሰብ የገዢው ፓርቲ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ሲገልጹ ተስተውለዋል። በርካቶችም የፓርቲዎው አመራሮች ይውጡልን በማለት ፓርላማውም እንዲፈርስ ጠይቀዋል።

የጸጥታ ኃይሎች ተቃዋሚዎች ወደ ፓርላማው ቅጥር ግቢ እንዳይጉ ሲከለክሉና ወደ 'ቦርጊባ' አደባባይ እንዳይሄዱ መንገድ ሲዘጉ ተስተውለዋል። ይህ ጎዳና በአውሮፓውያኑ 2011 ለተቀጣጠለው ጸረ መንግሥት ተቃውሞ ዋነኛ ማዕከል ሆኖ አገልግሎ ነበር።

ፖሊስ ተቃዋሚ ሰልፈኞቹን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ ጭምር የተጠቀመ ሲሆን አንዳንድ ሰዎችን ደግሞ በቁጥጥር ስር አውሏል። ይህን ተከትሎም ተቃውሞውም ወደ አብዛኛው የአገሪቱ ከተሞች ተስፋፍቷል።

ተቃዋሚዎችም የገዢው ፓርቲ ቢሮዎችን ሰብረው በመግባት ንብረቶችን የሰባበሩ ሲሆን 'ቶውዙር' ውስጥ የሚገኘው ያርቲው አካባቢያዊ ዋና ቢሮም በእሳት አያይዘውታል።

ፓርቲው በበኩሉ የሰልፈኞቹን ተግባር በማውገዝ ይህንን አጋጣሚ ወንጀለኛ ዘራፊዎች አገሪቱን ወደ ብጥብጥና መፈራረስ ለመውሰድ እየተጠቀሙበት ነው ብሏል።

ምንም እንኳን በዋና ከተማዋ ወጥተው ከተቃዋሚ ሰልፈⶉች ጋር አብረው ቢታዩም ፕሬዝዳንቱ ከዚህ በኋላ አላስፈላጊ አመጽ የሚቀጥል ከሆነ መከላከያ ኃይል ጣልቃ እንደሚገባ አስጠንቅቀዋል።

"ማንኛውም ዜጋ የጦር መሳሪያ የሚጠቀም ከሆነ፣ ጥይት የሚተኩስ ከሆነ የመከላከያ አባላት በጥይት ምላሽ ይሰጣሉ" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ከአስር ዓመታት በፊት በቱኒዚያ የተቀሰቀሰው አብዮት ተስፋፍቶ የአረብ አገራትንም ያዳረሰ ሲሆን በወቅቱም ከለውጡ በኋላ በርካታ ነገሮች እንደሚቀየሩ ተስፋ ተደርጎ ነበር።

ነገር ግን ቱኒዚያ አሁንም ድረስ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ የምትገኝ ሲሆን በአፍሪካም በኮሮረናቫይረስ በእጅጉ ከተጠቁት አገራት መካከል ትገኝበታለች።