የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት እጃቸውን ለፖሊስ ሰጡ

ጃኮብ ዙማ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታትሟል

የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ በፍርድ የተበየነባቸውን የእስር ቅጣት ለመጀመር ራሳቸውን ለፖሊስ አስረክበዋል።

ትላንት [ረቡዕ] ረፋድ ላይ ከመኖሪያ ቤታቸው አቅራቢያ ወደሚገኝ አንድ እስር ቤት እንዳመሩ ፋውንዴሽናቸው አስታውቋል።

የ79 ዓመቱ ዙማ ይህንን ባያደርጉ ኖሮ ፖሊስ አመሻሹ ላይ በቁጥጥር ስር ለማዋል እንደሚገደድ አስጠንቅቆ ነበር።

ዙማ አንድ የሙስና ምርመራ ላይ ላለመሳተፍ አሻፈረኝ በማለታቸው ነው የ15 ወራት እስር የተፈረደባቸው።

ፍርዱ በደቡብ አፍሪካ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ የሕግ ጥያቄ ያስነሳ ሲሆን ፣የቀድሞ ፕሬዝዳንት በተሰጠ የቀንና የሰዓት ገደብ እስከ ረቢእ እኩለ ለሊት በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ውሳኔን ያሳለፈ ነበር።

ቀነ ገደቡ የተቀመጠው ዙማ ባለፈው እሁድ እጃቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ተከትሎ ነው። እናም ያቋቋሙት ፋውንዴሽን ባወጣው አጠር ያለ መግለጫ "ፕሬዚዳንት ዙማ የእስር ማዘዣ ትዕዛዙን ለማክበር ወስነዋል" ብሏል።

ልጃቸው ዱዱ ዙማ በትዊተር ገጻ ላይ አባቴ "[ወደ እስር ቤቱ] እያቀና እንደሆነና አሁንም ጠንካራ ስሜት እንዳለው" አስፍሯል።

ጃኮብ ዙማ በደቡብ አፍሪካ ለእስር የተዳረጉ የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት ናቸው።

የቀድሞ ፕሬዝደንት ዙማ በዘጠኝ ዓመት የሥልጣን ዘመናቸው በሙስና ላይ ምርመራ በተደረገበት ወቅት ማስረጃ ለመስጠት የተሰጠውን መመሪያ ባለማክበራቸው ነበር 15 ወራት በእስር ቤት እንዲቆዩ የተወሰነባቸው።

በስልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ በውሳኔ አሰጣጡ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ከሌሎች ፖለቲከኞች ጋር አሲረዋል በሚል ነበር የተከሰሱት፡፡

ይህንን ክስ የማይቀበሉት ዙማ ግን የፖለቲካ ሴራ ሰለባ እንደሆኑ ደጋግመው ተናግረዋል።

ዙማ ምንም እንኳን በተመሳሳይ ምክንያት ከፓርቲያቸው ተገለው ከስልጣን ቢወርዱም በትውልድ ስፍራቸው ግን ጠንካራ ድግፍ አላቸው።

ለዚህም ይመስላል ዙማ ወደ ፍርድ ቤት ከማምራታቸው በፊት ከላላ በሚል በርከት ያሉ ሰዎች በመኖሪያ ቤታቸው አቅራቢያ የተሰባሰቡት።