የሄይቲን ፕሬዚዳንት በመግደል የተጠረጠሩ አራት ሰዎች በፖሊስ ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የሄይቲውን ፕሬዚዳንት ጆቬኔል ሞይሴን በመግደል የተጠረጠሩ አራት ሰዎች ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በነበረ የተኩስ ልውውጥ መገደላቸውን ፖሊስ አስታውቋል።
ሁለቱ በቁጥጥር ስር ሲውሉ ሌሎች ተጠርጣሪዎች ደግሞ በመዲናዋ ፖርት ፕሪንስ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር መፋጠጣቸው ተገልጿል።
"ተጠርጣሪዎቹ ይገደላሉ ወይ ይያዛሉ" በማለት የፖሊስ ኃላፊው ሊዎን ቻርለስ ተናግረዋል።
ታጣቂዎች ረቡዕ እለት የፕሬዚዳንቱን መኖሪያ ቤት ሰብረው በመግባት የ53 አመቱ ፕሬዚዳንት ጆቬኔልን ሲገድሉ ባለቤታቸውን አቁስለዋል።
ማንነታቸው ያልታወቁት እነዚህ ታጣቂዎች በፖርት ፕሪንስ ወደሚገኘው የፕሬዚዳንቱ የግል መኖሪያ ቤት የገቡት በአገሬው ሰዓት አቆጣጠር ከቀኑ ሰባት ሰዓት ነው።
በተተኮሰባቸው ጥይት ፕሬዚዳንቱ ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን ቀዳማዊት እመቤት ማርቲን ሞይዝ በህይወት ተርፈው ህክምና እንዲደረግላቸው ወደ ፍሎሪዳ ተወስደዋል።
ቀዳማዊት እመቤቷ ህይወታቸው በአስጊ ሁኔታ ላይ መሆኑም ተገልጿል።
"አራት ቅጥረኞች ተገድለዋል ሁለቱን በቁጥጥር ስር ማዋል ችለናል" ብለዋል የፖሊስ ኃላፊው ሊዎን ረቡዕ ረፋድ ላይ በቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ
አክለውም "ታግተው የተወሰዱብን ሶስት ፖሊሶች ደግሞ ማስለቀቅ ችለናል። ተጠርጣሪዎቹ የወንጀል ድርጊቱን ከፈፀሙበት ስፍራ ሲወጡ መንገዳቸውን ዘግተናል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከእነሱ ጋር እየታገልን እንገኛለን" ብለዋል።
ከፕሬዚዳንቱ ግድያ በኋላ የአገሪቱ ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር ክላውድ ጆሴፍ አገሪቷ እንድትረጋጋ ጠይቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም አውጀዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ስብሰባዎችን የማገድ፣ የፖሊስ ኃይልን በተፈለገው መንገድ መጠቀምና ሌሎች ተግባራትን ማከናወን ያስችላል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ግድያውን "አሰቃቂ" ያሉት ሲሆን ለሄይቲ ህዝብም መፅናናትን ተመኝተዋል።
የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በበኩላቸው "አረመኔያዊ ተግባር" ብለው የጠሩት ሲሆን መረጋጋትም እንዲሰፍን ጠይቀዋል።
ፕሬዚዳንት ጆቬኔል በሄይቲ መንበረ ስልጣኑን የተቆጣጠሩት በአውሮፓውያኑ 2017 ሲሆን በቅርብ ጊዜያትም ከስልጣን እንዲለቁ የሚጠይቁ በርካታ ተቃውሞዎችን አስተናግደዋል።












