ታዋቂው አሜሪካዊ ተዋናይ ቢል ኮዝቢ የእሥር ጊዜውን ሳይጨርስ ተለቀቀ

Bill Cosby

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታትሟል

አሜሪካዊው ኮሜዲያን ቢል ኮዝቢ የፔንሲልቬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተወሰነበት ብይን እንዲሻር ከወሰነ ከሰዓታት በኋላ ከእሥር ተለቀቀ።

የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዳኞች ከዚህ በፊት በነበረው ፍርድ "የአካሄድ ጥሰት" አለ ሲሉ ተደምጠዋል። ነገር ግን ዳኞቹ ይህ ውሳኔያቸው ያልተለመደ መሆኑን አልካዱም።

የ83 ዓመቱ ኮዝቢ ከሶስት እስከ 10 ዓመት ድረስ ከርቸሌ እንዲከርም ተፈርዶበት እንደነበር አይዘነጋም።

ተዋናዩ ሁለቱን ዓመት እስር ፊላደልፊያ በሚገኝ ማረሚያ ቤት አሳልፏል።

ኮዝቢ፤ በፈረንጆቹ 2018 ኮዝቢ የቀድሞዋን ቅርጫት ኳስ ተጫዋች አንድሪያ ኮንስታንድን በመድኃኒት መርዞ ወሲባዊ ጥቃት ፈፅሞባታል ተብሎ ነው እሥር የተበየነበት።

ኮዝቢ በተለይ በ1980ዎቹ ታዋቂ በነበረው ዘ ኮዝቢ ሾው በተሰኘው ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ምክንያት ነው የዝና ጣራን የነካው።

በአንድ ወቅት "የአሜሪካ አባት" የሚል ቅጥያ ተሰጥቶት የነበረው ኮዝቢ በርካታ ሴቶች ወሲባዊ ጥቃት አድርሶብናል ብለው ቢወቅሱትም በይፋ የተከሰሰው ግን በቅርጫት ኳስ ተጫዋቿ ኮንስታንድ ጉዳይ ነው።

ፍርዱ በተሰጠበት ወቅት ሚቱ [ #MeToo] ለተሰኘው በማሕበራዊ ድር አምባ ለተቀጣጠለው እንቅስቃሴ አንድ ድል ተደርጎ ተቆጥሮ ነበር።

ነገር ግን ረቡዕ ዕለት የፔንሲልቬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ ብይን ሲሰጥ "የአካሄድ ጥሰት" ተፈፅሟል ሲል ሰውዬው ፍርዳቸው እንዲሻር አድርጓል።

ዳኞቹ እንደሚሉት የኮዝቢ ጠበቆች ከበፊቱ አቃቤ ሕግ ጋር ኮዝቢ እንደማይከሰስ ተስማምተው ነበር።

ከዚህ ውሳኔ በኋላ የተለቀቀው ኮዝቢ በጉጉት ሲጠብቀው ወደ ነበረው የመገናኛ ብዙሃን አንጃ ሲራመድ ደከምከም ብሎ ታይቷል።

ኮዝቢ ለመገናኛ ብዙሃን ሰዎች ምንም ዓይነት ምላሽ ባይሰጥም የጠበቆቹ የበላይ የሆኑት አንድሩ ዋየት ቃላቸውን ሰጥተዋል።

"በዚህ ሞቃታማ ቀን - በጣም ሞቅ ያለ ፍርድ ነው የተሰጠን" ብለዋል ጠበቃው።

"ኮዝቢ ሁልጊዜም ስሙን ተጠቅሞ ሴቶችን ለማነቃቃት የሚሞክር ሰው ነው። እንዴት ሆኖ ነው አንድ በኤፍቢአይ ክትትል የሚደረግበት ሰው ሴቶችን የሚደፍረው የሚመርዘው? ሊያውም አንድ ጥቁር ሰው?" ብለዋል ጠበቃው።

የኮዝቢን ብይን ውድቅ ያደረጉት ዳኞች ባለ 79 ገፅ ትንታኔ ፅፈው አቅርበዋል።

እነሱ እንደሚሉት ከሆነ የቀድሞው አቃቤ ሕግ ኮዝቢ በኮንስታንድ ጉዳይ ምስክርነቱን የሚሰጥ ከሆነ አይከሰስም ቢሉም ከሰውታል።

አልፎም ምስክርነት ከሰጡት ሰዎች መካከል ከክሱ ጋር የማይገናኝ ምስክርነት የሰጡ ሰዎች አሉ ይላሉ ዳኞቹ።

ዳኞቹ ኮዝቢ ላይ ፍርደ ገምድል ውሳኔ ተሰጥቷል፤ እሱን መካስ የሚቻለው ብይኑ እንዲሻርና ከዚህ በኋላ እንዳይከሰስ በማድረግ ነው ይላሉ።

የኮዝቢ ብይን እንዲሰረዝ መደረጉ ከተሰማ በኋላ ሰዎች በሁለት ወገን ተከፍለው ሐሳባቸውን ይገልፁ ይዘዋል።

ዘ ኮዝቢ ሾው ላይ ሚስቱ ሆና የምትጫወተው ተዋናይት ፊሊሺያ ራሻድ "በስተመጨረሻም ፍትህ ፍትሃዊ ሆነች" ዓይነት ይዘት ያለው የደስታ መልዕክት በትዊተር ገጿ አስፍራለች።

የቀድሞው አቃቤ ሕግ ደግሞ "ማንም ሰው ታዋቂ ይሁን ሃብታም አሊያም ጉልበተኛ - ከሕግ በላይ አይደለም" ሲሉ ተደምጠዋል።

የኮዝቢ ከሳሾች የነበሩ ከ30 በላይ ሴቶችን የወከለችው ጠበቃ ግሎሪያ አልሬድ ውሳኔውን "አስደንጋጭ" ብላዋለች። ነገር ግን ውሳኔው የሰውየውን ድርጊት የሚሽረው አይደለም ስትል አክላለች።