ዩኬ በናይጄሪያው ተገንጣይ መሪ እስር ላይ እጄ የለበትም አለች

ንናምዲ ካኑ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ታትሟል

በደቡብ ምስራቅ ናይጄሪያ ተገንጣይ የሆነውን ቡድን የሚመራው ንናምዲ ካኑ ተላልፎ መሰጠትና እስሩ ላይ ተሳትፎ የለኝም ስትል ዩናይትድ ኪንግደም አስተባብላለች።

ንናምዲ የናይጄሪያና የእንግሊዝ ጥምር ዜግነት ያለው ሲሆን በአለም አቀፉ የወንጀለኞች አዳጅ ድርጅት ኢንተርፖል በቁጥጥር ስር የዋለው እሁድ እለት ነው።

የአገሪቱ ጠቅላይ አቃቤ ህግ እንዳስታወቀው ግለሰቡ ተገዶም ወደ ናይጄሪያም እንዲመለስ ተደርጓል።

በሃገር ክህደት ወንጀል ተከሶ የነበረው ንናምዲ በዋስ እያለም ነበር ከአራት አመት በፊት ከሃገር የወጣው።

መቀመጫውን በእንግሊዝ ለባለፉት አመታት አደርጓል ተብሎ የሚታመን ሲሆን በቁጥጥር ስር የዋለውም በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ነው የሚሉ መረጃዎችም እየወጡ ነው።

"ልናረጋግጥላችሁ የምንፈልገው ንናምዲ ካኑን ተላልፎ እንዲሰጥ በሚል በዩናይትድ ኪንግደም በቁጥጥር ስር አልዋለም" በማለት የእንግሊዝ ከፍተኛ ኮሚሽን ቃለ አቀባይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በናይጄሪያ ሚስጥራዊ ፖሊስ በቁጥጥር ስር እንዳለም የተገለፀ ሲሆን በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ ለአጭር ሰዓት ፍርድ ቤት ቀርቦ ነበር።

የግለሰቡ ፍርድ ሂደት ከአንድ ወር በኋላም ይጀመራል ተብሏል።

53 አመቱ ንናምዲ በናይጄሪያ እውቅና ማግኘት የጀመረው ራዲዮ ባያፍራ የተባለ ጣቢያ በአውሮፓውያኑ 2009 ከለንደን ሆኖ ማሰራጨቱን ተከትሎ ነው።

ሬድዮውንም በመጠቀም ለባያፍራ ነፃነት ይሟገት የነበረ ሲሆን ተከታዮቹንም ጦራቸውን አንስተው የናይጄሪያን መንግሥት እንዲታገሉ ጥሪ አቅርቧል።

ከአምስት አመታት በኋላም ኢንዲጂኒየስ ፒፕል ኦፍ ባያፍራ (ኢፖብ) የተባለ ድርጅት መሰረተ። የናይጀሪያ ባለስልጣናትም ድርጅቱን አሸባሪ ብለውታል።

በአውሮፓውያኑ 2015 ንናምዲ በቁጥጥር ስር ሲውል ከፍተኛ ተቃውሞን አስነስቶ ነበር።

ንናምዲ የኢቦ ቀደምት ህዝቦች መገንጠል አለባቸው በሚል እንቅስቃሴ መጀመሩ አዲስ ነገር አይደለም።

በአውሮፓውያኑ 1967 የኢቦ መሪዎች በባያፍራ ግዛት ነፃነት አውጀው ነበር። ነገር ግን የእርስ በርስ ጦርነቱን ተለትሎ በሚሊዮን የሚቆጠር ነዋሪም ሞቷል፤ ተገንጣዩም ቡድን ተሸንፏል።

ሆኖም ይህ ሃሳብ ሙሉ በሙሉ አልሞተም፤ ከአመታት በኋላም አንሰራርቷል። ኢቦፕ ኢስተርን ሴኩሪቲ ኔትወርክ የተባለ የጦር ክንፍ በባለፈው አመት ያቋቋመ ሲሆን ባለስልጣናቱ በፖሊስ ጣቢያዎችና ሌሎች የመንግሥት ተቋማት ጥቃት አድርሷል በማለት ይወነጅሉታል።

ፕሬዚዳንት ሙሃማዱ ቡሃሪ ኢፖብን እንደሚያፈራርሱት ቃል ገብተዋል።