የእስራኤል ሚኒስትር የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ጉብኝት ታሪካዊ ነው ተባለ

ታትሟል

የእስራኤል ሚኒስትር በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የሚያደርጉት ታሪካዊ ጉብኝት የሁለቱን አገራት ጥብቅ ግንኙነት አመላካች መሆኑ ተገለፀ።

የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያር ላፒድ ማክሰኞ ዕለት የተባበሩት አረብ ኤምሬትስን ምድር ሲረግጡ ለአገራችውና ለአረቡ ዓለም ታሪካዊ አጋጣሚ ይሆናል ተባለ።

ላፒድ ከ9 ወራት በፊት እስራኤል፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና ባህሬን ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ከተስማሙ በኋላ በባህረ ሰላጤ አገራት ይፋዊ ጉብኝት በማድረግ የመጀመሪያው የእስራኤል ሚኒስተር ይሆናሉ።

በሁለቱ ቀናት ጉብኝትም ሚኒስትር ላፒድ፤ ከዩኤኢ አቻቸው ሸክ አብዱላህ ቢን ዛይድ አል ናህያን ጋር ይገናኛሉ። የእስራኤል ኤምባሲንና የቁንስላ ጽ/ቤት በአቡዳቢና በዱባይ መርቀው ይከፍታሉ።

የሚኒስትሩ ጉብኝት ከእስራኤልና ጋዛ ግጭት በኋላ በሁለቱም ወገን የተደረገ የመጀመሪያው ይፋዊ ግንኙነት በመሆኑ ወሳኝ መሆኑ ተነግሯል።

እንደ ተባበሩት መንግሥታት ከሆነ ግንቦት ወር ላይ በተፈጠረ ግጭት በጋዛ ቢያንስ 256 ሰዎች ሲገደሉ፤ በእስራኤል ደግሞ 13 ሰዎች ተገድለዋል።

አሁን ለተጀመረው የአገራቱ ግንኙነት የ11 ቀናቱ ግጭት የመጀመሪያው ፈተና ነበር።

በተለይም የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች አመራር ስምምነቱን እስራኤል ፍልስጤማውያን በከፍተኛ ሁኔታ የተቃወሙትንና የዌስት ባንክን ክፍሎች ለመያዝ ያቀደችውን ዕቅድ ለመግታት እንደ አንድ አጋጣሚ ተጠቅመውበታል፡፡

እስራኤልና ፍልስጤም ወደ ግጭት ሲያመሩ ዩኤኢ በምስራቅ እየሩሳሌም የሚኖሩ የአይሁድ ሰፋሪዎችን እስራኤል ፍልስጥኤማዊያንን ማስወጣቷን አውግዛለች።

በእስራኤልና በፍልስጤም ውጥረቶች እንዲባባሱ የሚያደርጉ ምክንያቶችን እስራኤል እንድታረግብም አሳስባ ነበር።

ነገር ግን በግጭቱ ወቅት እስራኤል በጋዛ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶችን ስታዘንብ ዩኤኢ የአይሁድ መንግሥት ላይ ጫና ለማሳደር ያደረገችው ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ እምብዛም ነበር።

አሁን ላይ ከአንባገነኗ ዩኤኢ ጋር ስላለው ፖለቲካዊ ጉዳይ የሕዝቡን ስሜት መለካት አስቸጋሪ ቢሆንም የእስራኤልን ድርጊት የሚያወግዝና ለፍልስጤማዊያን ድጋፍ የሚያሳዩ መልዕክቶች በማህበራዊ ሚዲያ እየተጋሩ ነው።

ተቀማጭነቱን ዱባይ ያደረገው የፖለቲካ ተመራማሪ አብዱልክሃላቅ አብዱላህ የሚኒስትር ላፒድ ታሪካዊ ጉብኝቱ ሁለቱ አገራት ያጋጠማቸውን ፈተና በደንብ እንደተቋቋሙ የሚያሳይ ነው ብለዋል።

"የሁለትዮሽ ግንኙነቱ የመጀመሪያውን ፈተና አልፏል፤ ይህም እንደማይቀለበስ ያሳያል" ብለዋል የፖለቲካ ተመራማሪው።

ተማራማሪው ዩኤኢ ሁለት መንገዶችን እየተከተለች መሆኑን ጠቅሰው፤ አንደኛው ሁኔታውን ወደ ቀድሞው መመለስ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ፍልስጤማዊያን የራሳቸውን መንግሥት የመመስረት መብትን መደገፍ መሆኑን ተናግረዋል።