ምርጫ 2013፡ የምሥራቃዊ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ምርጫውን እንደሚታዘብ አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, EASF
የምሥራቃዊ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ሰኞ ዕለት የሚደረገውን አገራዊ ምርጫ የሚታዘቡ አባላቱ ኢትዮጵያ መግባታቸውን አስታወቀ።
የኃይሉ ዳይሬክተር ብርጋዲዬር ጀነራል ጌታቸው ሽፈራው ከኢትዮጵያ መንግሥት ምርጫውን የመታዘብ ጥያቄን ተቀብብሎ ተቋሙ የምርጫውን አፈጻጸም የሚታዘቡ ባለሙያዎችን ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ማድረጉን ገልጸዋል።
ተጠባባቂ ኃይሉ ቅዳሜ ዕለት አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኘው ጽህፈት ቤቱ በሰጠው መግለጫ፤ ከአባል አገራቱ የተወጣጡ 28 ባለሙያዎችን የምርጫውን አፈጻጸም በአምስት ክልሎች እና በሁለት የከተማ አስተዳደሮች ውስጥ ይታዘባል ተብሏል።
ኢስተርን አፍሪካ ስታንድባይ ፎርስ (ኢኤኤስኤፍ) በርካታ የምሥራቅ አፍሪካ አገራትን በአባልነት የያዘ ሲሆን ዋና ዓላማውም በምሥራቅ አፍሪካ ቀጠና ሰላም እና ደኅንነት እንዲረጋገጥ የሚሰራ መሆኑ ተጠቅሷ።
የሠራዊት፣ የፖሊስ እና የሲቪል አካላትን በውስጡ አቅፎ የያዘው ይህ ኃይል፤ የጸጥታ አስከባሪ ኃይልን በፍጥነት በማሰማራት የሰላም ማስከበር ተልእኮዎችን መደገፍ እና ሰላምን ለማረጋገጥ በተለያዩ አገራት በጥምረት የተመሰረተ ነው።
የተቋሙ ምርጫ ታዛቢ ቡድን የሚንቀሳቀስባቸው ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች ኦሮሚያ፣ አማራ፣ አፋር፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች፣ ድሬ ደዋ እና አዲስ አበባ ናቸው።
የባለሙያ ቡድኖቹም ከቡሩንዲ፣ ከጂቡቲ፣ ከኬንያ፣ ከሶማሊያ፣ ከሲሼልስ፣ ከኡጋንዳ፣ ከሩዋንዳ እና ከኮሞሮስ የተወጣጡ ናቸው።
ቡድኑ የምርጫውን አፈጻጸም የሚገመግመው እአአ 2012 የረቀቀውን የአፍሪካ ሕብረት የዲሞክራሲ ቻርተር፤ ምርጫ እና አስተዳደር፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት/የአፍሪካ ሕብረት የምርጫ አፈጻጸም መርኅ በአፍሪካ እንዲሁም የኢትዮጵያ የምርጫ ሕጎች ላይ መሠረት ባደረገ መልኩ እንደሚሆን ገልጿል።
የጂቡቲ ዜግነት ያላቸው አምባሳደር አበዲላህ ኦውሌድ አሊ የምርጫ ታዛቢ ቡድኑን ይመራሉ ተብሏል።
አምባሳደር አበዲላህ የምርጫ ታዛቢ ቡድኑ ምርጫውን የሚታዘበው እአአ 2002 ላይ የረቀቀውን የአፍሪካ ሕብረት ምርጫ ታዛቢዎች የሥነ-ምግባር ደንብን መሠረት በማድረግ መሆኑን ጠቅሰው ይህ የሥነ-ምግባር ደንብ የተቀረው ዓለም ከሚመራበት መርኅ ጋር ተመሳሳይ መሆኑን አውስተዋል።
ይህ የሥነ-ምግባር ደንብ ተጥሶ ቢገኝ ተቋሙ የምርጫ ታዛቢዎቹን ወደ ማዕከሉ እስከመጥረት የሚደርስ ጠንካራ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቀዋል።
አምባሳደሩ ጭምረውም በምርጫው ማግስት ማለትም ሰኔ 15/2013 ዓ.ም የምርጫ ታዛቢዎች የመጀመሪያ ሪፖርት ይፋ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
ቡድኑ ይህን ምርጫ የሚታዘበው የዲሞክራሲ ግንባታ ሂደትን ለመደገፍ፣ የዓለም አቀፍ ደረጃን በጠበቀ መልኩ ምርጫውን ታዝቦ ወቅታዊ እና ገለልተኛ የሆነ የምርጫ ሂደት ሪፖርትን መስጠት የሚሉ ዓላማዎችን በመያዝ መሆኑ ተገልጿል።
በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች ነገ ሰኞ ሰኔ 14/2013 ዓ.ም የሚካሄደውን ስድስተኛውን የኢትዮጵያ አገራዊ ምርጫ በመታዘብ በኩል የተለያዩ ተቋማትና ማኅበራት ይሳታፋሉ ተብሏል።















