ሀማስን ትጥቅ አስፈትቶ ጋዛን መልሶ መገንባት ይቻላል?

ታትሟል

ረዥም ርቀት ተጓዥ ሮኬቶች፣ ሚሳኤሎች፣ ሰው አልባ ትንንሽ አውሮፕላኖች እና ሙሉ ወታደራዊ ትጥቅ ያነገቡ የሀማስ ተዋጊዎች ከእስራኤል ጋር ካለው ግጭት ጋር ተያይዞ በጋዛ ሰርጥ ትልቅ ወታደራዊ ትዕይንት አካሂደዋል።

በአሜሪካ፣ በእስራኤል፣ በአውሮፓ ሕብረት እና በሌሎችም እንደ ሽብርተኛ ቡድን የሚቆጠረው ሀማስ፤ መሰል ተግባራትን በተደጋጋሚ ይፈጽማል።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለጋዛ ነዋሪዎች ሊያደርገው የሚችለው ድጋፍ ላይ ትልቅ ደንቃራ እንደሆን በርካቶች እየገለጹ ነው።

የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ዶሚኒክ ራብ በቅርቡ እየሩሳሌምና ዌስት ባንክን የጎበኙ ሲሆን፤ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚያደርገው ድጋፍ ለሀማስ መሣሪያ መግዣና መንቀሳቀሻ ሳይሆን በፍልስጤም ሕዝቦችና ችግሮቻቸው ላይ እንዲውል ማድረግ በጣም ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ጋዛን የሚያስተዳድረው ታጣቂው ቡድን ሀማስ ደግሞ እስራኤል በአካባቢው ምንም አይነት መብት እንደሌላት በጽኑ ያምናል።

የተባበሩት መንግሥታት ያወጣው መረጃ እንደሚጠቁመው፤ በቅርቡ በተነሳው ግጭት ሳቢያ ከ16 ሺህ በላይ ቤቶች ጋዛ ውስጥ የወደሙ ሲሆን፤ 58 ትምህርት ቤቶችና ማሰልጠኛ ማዕከላትም እንዳልነበሩ ሆነዋል።

በተጨማሪም ዘጠኝ ሆስፒታሎችና ወሳኝ የመሠረተ ልማት ተቋማትም ጉዳት ደርሶባቸዋል።

የእስራኤል መከላከያ በበኩሉ እስካሁን ባደረስኩት ጥቃት ከ1 ሺህ በላይ ታጣቂው የሚጠቀምባቸውን ቦታዎች ኢላማ አድርጌያለሁ ብሏል።

በጋዛ በደረሱ ጥቃቶች ቤት አልባ ከሆኑ በሺዎች ከሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን መካከል የካሊዲ ቤተሰብ አንደኛው ነው።

የእስራኤል የጦር አውሮፕላኖች ሰፈራቸውን ኢላማ አድርገው ጥቃት ሲፈጽሙ ቤታቸው፣ መንደራቸውና በዙሪያቸው ያሉ ነገሮች በሙሉ ወድመዋል።

"የወንድ ልጄ መጫወቻ በስብርባሪ ጠርሙስ ተወጋግቶ ተመለከትኩ። የደረሰውን ጉዳት ሳስተውል በጣም አለቀስኩ" ትላለች በአሁኑ ወቅት ከባለቤቷ እና ልጇ ጋር በዘመድ ቤት ተጠልላ የምትገኘው ዋድ አል ካሊዲ።

"ምናልባት ጦርነቱ አብቅቶ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን እኛ መልሶ መገንባት የሚያስችል ገንዘብ የለንም። በጣም የሚያምረው ቤታችን ውስጥ ተመልሶ መኖር ነው የምፈልገው" ብላለች።

የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው፤ ለሳምንታት በዘለቀው የእስራኤልና ፍልስጤም ግጭት ምክንያት ቢያንስ 256 ሰዎች ጋዛ ውስጥ የተገደሉ ሲሆን፤ በእስራኤል በኩል ደግሞ 13 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል።

የእስራኤል መከላከያ በበኩሉ ከሟቾች መካከል 200 የሚሆኑት የሀማስ ታጣቂዎች እንደሆኑ ያስታወቀ ቢሆንም፤ ሀማስ ግን 80 ተዋጊዎቼ ብቻ ናቸው የተገደሉብኝ ይላል።

እስራኤልና ግብጽ ጋዛ ላይ በጣሉት የመሬትና የውሃ ላይ እንቅስቃሴ ገደብ ምክንያት ጋዛን መልሶ ማቋቋም በጣም ፈታኝ እንደሚሆን ከወዲሁ ተፈርቷል።

ሁለቱ አገራት ይህንን ማዕቀብ የጣሉት በአውሮፓውያኑ 2007 ላይ ሀማስ ከፍልስጤም ባለሥልጣናት ላይ አነስተኛ ስፋት ያለው አካባቢ መውሰዱና መቆጣጠሩን ተከትሎ ነው። ከአንድ ዓመት በኋላ ግን ቡድኑ በአጠቃላይ ምርጫ በማሸነፍ በይፋ ጋዛን ማስተዳደር ጀምሯል።

ሀማስ በመቋቋሚያው ቻርተር ላይ "ለእስራኤል መውደም ሳልታክት እሠራለሁ" የሚል አንቀፅ አስፍሯል።

ሀማስ ሲመሰርት ሁለት ዓላማዎች ነበሩት። አንደኛው በጦር ክንፉ እስራኤልን መውጋት ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ ኢዘዲን አል-ቃስም በሚሰኘው ማዕቀፉ ለፍልስጤማውን ማኅበራዊ አገልግሎት መስጠት ነው።

እአአ 2005 ላይ እስራኤል ጦሯን እና ሰፋሪዎቿን ከጋዛ ስታስወጣ፤ ሀማስ በፍልስጤም ፖለቲካ ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ ማድረግ ጀመረ። ከአንድ ዓመት በኋላ በተካሄደ ምርጫም ሰፊ ድምጽ ማግኘት ችሎ ነበር።

የሀማስ ተዋጊዎች ከእስራኤል ጋር ሦስት ጦርነቶችን ተዋግተዋል። የሀማስ የጦር ክንፍ በእስራኤል፣ በአሜሪካ፣ በአውሮፓ ሕብረት እና በዩናይትድ ኪንግደም አሸባሪ ቡድን ተብሎ ተፈርጇል።

ማዕቀቡ የአካባቢውን ምጣኔ ሀብት በእጅጉ ያሽመደመደ ቢሆንም አገራቱ ግን ማሳካት የቻሉት የደኅንነት ኢላማቸው እምብዛም አይደለም። ዋናው የማዕቀቡ ኢላማ መሣሪያዎች ወደ ጋዛ እንዳይገቡና ቡድኑ እንዲዳከም ነበር።

ለተከታታይ 11 ቀናት በቆየው የለየት ፍጥጫ የእስራኤል ወታደሮች 4 ሺህ 300 ሮኬቶች ወደተለያዩ ከተሞች ከጋዛ እንደተተኮሰባቸውና በርካታ መኖሪያ ቤቶችና መሠረተ ልማቶች እንደወደሙ ገልጸዋል።

በአውሮፓውያኑ 2014 ላይ ባጋጠመ ተመሳሳይ ግጭት እስራኤል በወሰደችው እርምጃ እስከ 2251 ፍልስጤማውያን ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን፤ ከነዚህ መካከል 1462 ንጹሀን ዜጎች ናቸው። በእስራኤል በኩል ደግሞ 67 ወታደሮች የተጎዱ ሲሆን፤ ስድስት ንጹሀን ዜጎችም ሕይወታቸው አልፏል።

"እራሳቸውን መልሰው በማቋቋም ከበፊት በተሻለ መልኩ ረዥም ርቀት መጓዝ የሚችሉ ሮኬቶችና ትልልቅ ከባድ መሣሪያዎች ታጥቀዋል" ይላሉ የቀድሞው የእስራኤል ሠራዊት ብርጋዲየር ጀነራል ማይክል ሄርዞግ።

2014 ላይ ግብጽ ሮኬቶችና ሚሳኤሎች በድብቅ ወደ ጋዛ የሚገቡባቸው መተላለፊያ ቱቦዎች ላይ በወሰደችው እርምጃ በርካታ መሠረተ ልማቶች ወድመው ነበር። ከኢራን ወደ ጋዛ ይገቡ የነበሩ ከባድ መሣሪያዎች ቁጥር ደግሞ በእጅጉ ቀንሶ ነበር።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ ሀማስ መሣሪያዎቹን ከኢራን ከማስመጣት ይልቅ ባለሙያዎቹን ከኢራን አስመጥቶ መሣሪያዎቹን መሥራት ላይ ትኩረቱን አድርጓል። በዚህም በርካታ ሮኬቶች የሚሠሩት እዛው ጋዛ ውስጥ ነው።

"ችግር ሁሌም ብልሀትን ይወልዳል። ሀማስም መሣሪያዎችን ለማስገባት ፈተና ሲገጥመው የፈጠረው አማራጭ ቢኖር እዛው መሣሪያዎቹን ማምረት ነው" ይላሉ የቀድሞ ጀነራሉ።

እስራኤል ከመሣሪያዎች በተጨማሪ ከአንድ በላይ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ እንደ ሲሚንቶ፣ ብረት፣ ቱቦዎችና ሌሎች እቃዎች ወደ ጋዛ በብዛት እንዳይገቡ ከፍተኛ ቁጥጥር ታደርጋለች።

ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ሀማስ ሮኬቶችና ሌሎች የጦር መሣሪያዎችን ለመሥራት በብዛት የሚጠቀመው እነዚህን ቁሳቁሶች ስለሆነ ነው።

ግብጽም ብትሆን ለመሰል ተግባራት ሊውሉ የሚችሉ ግብአቶች ላይ ክልከላና ኮታ ጥላለች።

ነገር ግን እነዚህን ሁሉ ክልከላዎች አልፎ ቡድኑ አሁንም ሮኬቶችን እያመረተና እያስወነጨፈ ይገኛል።

የእስራኤል መከላከያ ኃይልም በ11 ቀናቱ ግጭት በበርካታ ሚሊየን ዶላሮች የተገነባና ከ100 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያለው የሀማስ ማስተላለፊያ ቱቦ ላይ ድብደባ መፈጸማቸውንና ማፈራረሳቸውን አስታውቋል።

ሁለቱ ወገኖች የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረጋቸው ባለፈው ወር ይፋ ሲደረግ በርካቶች ደስታቸውን ገልጸው ነበር።

ተኩስ አቁሙ ከተተገበረ በኋላ በርካታ ፍልስጥኤማዊያን በጋዛ ጎዳናዎች ላይ ደስታቸውን ለመግለጽ የወጡ ሲሆን፤ አንድ የሀማስ ባለሥልጣን "አሁንም መሳሪያችንን እንዳቀባበልን ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።

ከመስጊዶች የሚሰሙ የድምፅ ማጉያዎች "በእየሩሳሌሙ ሰይፍ ውጊያ ትግላችን ድል አስገኝቷል" የሚሉ መልክቶችን አስተጋብተዋል።

ሁለቱም አካላት በፍልሚያው አሸናፊነታቸውን አውጀዋል። የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን የተኩስ አቁሙ "ለለውጥ እድል የሚሰጥ ነው" ሲሉ ስምምነቱን ገልጸውታል።

የእስራኤል ካቢኔ የተኩስ አቁሙን ሐሳብ በሙሉ ድምፅ ማፅደቁን ገልጿል። "የፖለቲካ ክፍላችን የዘመቻው ቀጣይነት የሚወሰነው መሬት ላይ ባለው ሁኔታ ነው ሲል አፅንኦት ሰጥቷል" ሲልም አክሏል።

የእስራኤሉ የመከላከያ ሚኒስቴር ቢኒ ጋንትስ የጋዛው ጥቃት "ያልተጠበቁ ትርፎችን አስገኝቶልናል" ሲሉ በትዊተር ገፃቸው ላይ አስፍረዋል።

አንድ የሀማስ ባለሥልጣን ለአሶሺየትድ ፕሬስ እንደገለጹት፤ እስራኤል የተኩስ አቁም ማድረጓ እንደ ትልቅ ድል የሚቆጠር እና ይህም ለእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒናሁ ሽንፈት ነው።

ነገር ግን በሀማስ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምክር ቤት አባል የሆኑት ባሴም ናይም ስለ ተኩስ አቁሙ ዘላቂነት ጥርጣሬ እንዳላቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።