ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በነዋሪዎች የተጨናነቀችው ጋዛ ስለምን በጉግል ካርታ ላይ ደብዝዛ ትታያለች?
ይህ ጉዳይ ለማንኛውም ግለሰብ ይፋዊ የሆነ መረጃን ተጠቅመው ጥቃት እና ውድመት የደረሰባቸውን አካባቢዎችን የሚከታተሉ ተመራማሪዎች ዐይን ውስጥ ከገባ ቆይቷል።
እነዚህን መረጃዎች ተጠቅሞ ምርምር የሚያደርገው ሳሚር "ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን የሳተላይት ምሥሎችን፤ በእስራኤል እና ፍልስጤም ድንበሮች አካባቢ ማግኘት አለመቻላችን ወደ ኋላ ጎትቶናል" ይላል።
በእስራኤልና በፍልስጤም ድንበር አካባቢ ምንም እንኳ ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ምሥሎችን የሚያቀርቡ ኩባንያዎች ቢኖሩም ጉግል ኧርዝ የተሰኘው መተግበሪያ ላይ የሚታየው የሳተላይት ምሥል ግን ጥራቱ የወረደ ነው።
እነዚህን ምሥሎች ተጠቅሞ በጋዛ ከተማ መኪኖችን ለመለየት እንኳን አዳጋች ነው።
ይህንን ከሰሜን ኮርያዋ ከተማ ፒዮንግያንግ ጋር ቢነጻጸር በከተማ የሚወሰዱ የሳተላይት ምሥሎች መኪኖችን እንዲሁም ግለሰቦችን በሚገባ መለየት ያስችላሉ።
የሳተላይት ምሥል ለምንድን ነው ያስፈለገው?
ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች የሳተላይት ምሥል እጅጉን ጠቃሚ ነው።
በመካከለኛው ምስራቅ ባለው ውጥረት እስራኤልና ጋዛ የሚያስወነጭፏቸው ሚሳዔሎች እና የሚመቷቸውን ሕንጻዎችን ለመለየት የሳተላይት ምሥሎች ሁነኛ መሣሪያዎች ናቸው።
ይሁን እንጂ በበርካቶች ዘንድ ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኘው ጉግል ኧርዝ በጋዛ አካባቢ የሚታየው ምሥል ጥራቱ የወረደ በመሆኑ በሚገባ ምድር ላይ ያለውን የማያሳይ ነው።
የቢሊንግ ካት ጋዜጠኛው ኤሪክ ቶለር " ጉግል ኧርዝ ላይ ያለው የቅርብ ጊዜ ምሥል የተወሰደው በ2016 ነው እናም የሚረባ አይደለም። በሶሪያ የሚገኙ የተወሰኑ ገጠራማ አካባቢዎችን ቀረብ አድርጌ ለማየት ስሞክር ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ከ20 በላይ ምሥሎች በከፍተኛ ጥራት ተወስደዋል" ይላል።
ጉግል በበኩሉ ዓላማው "በጣም ጥግግት የበዛባቸው አካባቢዎችን በየጊዜው ምሥሎቹን ማደስ" እንደሆነ ቢናገርም ይህ ግን በጋዛ የተተገበረ አይመስልም።
ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ምስሥሎች አሉ?
የአሜሪካ መንግሥት የሳተላይት ምሥል የሚያቀርቡ ኩባንያዎች ላይ እስከ ባለፈው ዓመት ድረስ በእስራኤል እና ፍልስጤም ድንበር አካባቢዎች ጥራት ያለው ምሥል እንዳያቀርቡ ክልከላ አስቀምጦ ነበር።
ይህ ገደብ የተጣለው በእስራኤል አሳሳቢነት ሲሆን በዚህም የተነሳ የአሜሪካ ኩባንያዎች በአካባቢው ዝቅተኛ ጥራት ያላቸው ምሥሎችን ብቻ እንዲያቀርቡ ይገደዳሉ።
እንዲህ አይነት ገደቦች የጦር ካምፖች ባለባቸው አካባቢዎች የተለመዱ ቢሆንም ነገር ግን አንድ አገር ሙሉ በሙሉ ጥራቱ የወረደ የሳተላይት ምሥል ሲኖራት ጋዛ የመጀመሪያዋ ነች።
ሕጉ እስራኤልን ብቻ ቢጠቅስም የፍልስጤም ድንበር አካባቢዎችንም አካትቷል።
ይኹን እንጂ ከአሜሪካውያን ውጪ በባለቤትነት የተያዙ የሳተላይት ምሥል አቅራቢዎች ለምሳሌ የፈረንሳዩ ኩባንያ ኤርባስ በዚህ አካባቢ በከፍተኛ ጥራት የተነሱ ምሥሎችን ሊያቀርብ ይችላል።
በዚህም የተነሳ ከባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ጀምሮ አሜሪካ ይህንን ሕጓን እንድትሰርዝ ተገድዳለች።
አሁን የአሜሪካ ኩባንያዎች በአካባቢው ከፍተኛ ጥራት ያለው ምሥል ያቀርባሉ።
ታዲያ አሁንም ምሥሎቹ ለምን ጥራት ሳይኖራቸው ቀሩ?
ቢቢሲ ጉግልን እና አፕልን ያነጋገረ ሲሆን አፕል በቅርቡ በአካባቢው ያሉትን ምሥሎቹን ከፍተኛ ጥራት ወዳላቸው ለማሻሻል እየሰራ መሆኑን ተናግሯል።
ጉግል በበኩሉ ምሥሎቹን ከተለያዩ አካላት እንደሚሰበስብ ገልጾ "ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ምሥሎች በቀረቡ ወቅት ይስተካከላል" ብሏል።
አክሎም "አሁን ግን የማጋራት ሃሳብ እንደሌለው" አስታውቋል።
እነዚህን ምሥሎች የሚያነሳቸው ማን ነው?
ጉግል ኧርዝ እና አፕል ማፕስ ምሥሎቻቸውን የሚወስዱት ከሳተላይት ምሥል አቅራቢ ድርጅቶች ነው።
ማክሳር እና ፕላኔት ላብስ ሁለት ትልልቅ የሳተላይት ምሥል አቅራቢ ሲሆኑ በእስራኤል እና ጋዛ ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን ምሥሎች ያቀርባሉ።
ሁለቱም ኩባንያዎች በአሜሪካ ተጥሎ የነበረው እገዳ ከተነሳ ወዲህ በአካባቢው ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ምሥሎች እያቀረቡ መሆኑን አስረድተዋል።
ነገር ግን ለሕዘብ ክፍት የሆነን መረጃ በነጻ በመውሰድ የሚጠቀሙ ተመራማሪዎች የሚገለገሉባቸው መተግበሪያዎች በነጻ የሚገኙትን ብቻ በመሆኑ ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ምሥሎችን ማግኘት አዳጋች ያደርግባቸዋል።
ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ምሥሎች ምን ይረዳሉ?
በሂውመን ራይትስ ዎች የሚገኙ ተመራማሪዎች በ2017 በሚየንማር ወታደሮች በሮሂንጃ ሙስሊሞች መንደር ላይ የደረሰውን ጥቃት ያጋለጡት የሳተላይት ምሥልን ተጠቅመው ነው።
ይህ መረጃ ወደ ባንግላዲሽ ተሰድደው ከነበሩ የሮሂንጅያ ሙስሊሞች ከሰጡት መረጃ ጋር ተጣጥሟል።
የሳተላይት ምሥል በቻይና ሙስሊሞች ላይ የሚደርሰውን የጉልበት ብዝበዛ ለመለየት በብርቱ ማገዙ ይነገራል።
ቻይና "የዕደ ጥበብ ማሰልጠኛ" በሚል ሽፋን ሙስሊሞችን የምታጉርበት ካምፕ ዢንዣንግ በሚሰኘው የምዕራብ ቻይና ክፍለ ግዛት ዳባቼንግ በምትባል ትንሽዬ አውራጃ ውስጥ ይገኛል።
ቻይና "የአክራሪ ሙስሊሞች ሞገደኛ አስተሳሰብ የምገራበት ከፍተኛ የትምህርትና ሥልጠና ተቋሜ ነው" ስትል ማስተባበሏ ይታወሳል።።