ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እየሩሳሌም፡ በፍልስጤማዊያንና በእስራኤል ፖሊስ መካከል የተነሳው ግጭት አገርሽቷል
በፍልስጤማዊያንና በእስራኤል ፖሊስ መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት ቀጥሎ ትላንት [ቅዳሜ] ምሽት እየሩሳሌም ስትናጥ አምሽታለች።
ተቃዋሚዎች የፖሊስ ኃይል ላይ ድንጋይ ወርውረዋል፤ ኦልድ ሲቲ ውስጥ የሚገኘውን የደማስቆ በር በእሣት አቃጥለዋል።
ፖሊስ በምላሹ ግፊት ባለው ውሃና በፈንጂ ቁሳቁስ ተቃዋሚዎችን ለመበታተን ሞክሯል።
በቅዳሜው ግጭት የፍልስጤም አደጋ ጊዜ ሕክምና ሰጪ እንዳለው ቢያንስ 90 ፍልስጤማዊያን ቆስለዋል። የእስራኤል ፖሊስ ደግሞ አንድ ፖሊስ መኮንኔ ተጎድቶብኛል ብሏል።
አይሁድ ሰፋሪዎች መሬቱ የኛ ነው ብለው በሥፍራው የነበሩ ፍልስጤማዊያንን ሊያስነሱ ይችላሉ መባሉን ተከትሎ ነው ተቃወሞው የተቀሰቀሰው።
አርብ ዕለት አል-አስቃ መስጂድ አካባቢ በተከሰተው ግጭት ከ200 በላይ ፍልስጤማዊያንና ቢያንስ 17 የእስራኤል ፖሊሶች መጎዳታቸውን የአደጋ ጊዜ ሰዎችና ፖሊስ አስታውቋል።
ምንም እንኳ አል-አስቃ መስጂድ ለወትሮው ውጥረት የሚገግስበት ሥፍራ ቢሆንም የአርቡ ግጭት ግን በጣም አስከፊው ነበር ተብሏል።
የመካከለኛው ምስራቅ አደራዳሪዎች ማለትም ዩናይትድ ስቴትስ ሩስያና የተባበሩት መንግሥታት ቅዳሜ ዕለት በግጭቱ የተሰማቸውን "ጥልቅ ሐሳብ" ገልፀዋል።
በሌላ ዜና ቅዳሜ ዕለት የእስራኤል ጦር በሃማስ ከምትመራው የጋዛ ሰርጥ ከፍልስጤም አማፂያን ሮኬት ተተኩሶብኛል ብሏል።
የእስራኤል ጦር "በምላሹ አየር ኃይላችን ደቡባዊ ጋዛ ውስጥ ያለን የሃማስ ወታደራዊ ካምፕ መትተናል" ሲል በትዊተር ገፁ አስታውቋል።
የእስራኤል ጦር ስለክስተቱ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ቢቆጠብም የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን ግን ሮኬቱ ምንም ጉዳት ሳያደርስ ሜዳ ላይ ወድቋል ብለዋል።
የቅዳሜው ግጭት የተቀሰቀሰው የደማስቆ በር አካባቢ ሲሆን በሺህዎች የሚቆጠሩ አማኞች አል-አስቃ መስጅድ ከሰገዱ በኋላ ነው።
የፍልስጤም ቀይ ጨረቃ ቢያንስ 90 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ 14 ሰዎች ደግሞ ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን አሳውቋል።
ቅዳሜ ዕለት የእስራኤል ፖሊስ ወደ መስጅድ በባስ ሲሄዱ የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ አማኞችን አስቁሞ ነበር።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ሃገራቸው ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ ሕግና ሥርዓት በማስከበር የኃይማኖት ነፃነት እየጠበቀች እንዳለች ተናግረዋል።
የፍልስጤሙ መሪ ማሕሙድ አባስ የእስራኤልን ድርጊት "ሃጢያታዊ ጥቃት" ሲሉ ኮንነዋታል።