የደቡብ አፍሪካ ንጉሳዊ ቤተሰብ የተተኪነት ጥያቄ ወደ ፍርድ ቤት አመራ

ታትሟል

የደቡብ አፍሪካ ንጉሳዊ ቤተሰብ የተተኪነት ጥያቄ ወፍርድ ቤት አመራ

ህወታቸው ያለፈው የደቡብ አፍሪካው የዙሉ ንጉስ ጉድዊል ዝዌሊቲኒን ለመተካት በንጉሳዊው ቤተሰብ ውስጥ የተከሰተው ውዝግብ ወደ ፍርድ ቤት ማምራቱ ተዘገበ።

የሟቹ ንጉስ የመጀመሪያ ባለቤት የነበሩት ሲቦንግሊ ድላሚኒ የባለቤታቸው ኑዛዜ እንዲፈፀም ቢጠይቁም የንጉሱ የመጨረሻ ኑዛዜ ግን ተጭበርብሯል የሚሉ ክሶች እየቀረቡ ይገኛሉ።

ይህ የክስ ዜና የተሰማው ንግስት ሺኢዌ ማንትፎምቢ ዲላሚኒ ዙሉ ህወታቻው ማለፉን ተከትሎ ነው።

ንጉሱ በ72 ዓመታቸው ከስኳር በሽታ ጋር በተያያዘ ችግር ህይወታቸው ካለፈ በኋላ ንግስት ማንትፎምቢ ከአንድ ወር በፊት በአስተዳዳሪነት ተሹመው ነበር።

የንጉሱ የመጀመሪያ ባለቤት የንግስት ማንትፎምቢን ሹመት በመቃወም ክስ የመሰረቱ ሲሆን ፍርድ ቤቱ የእርሳቸውን ትዳር በብቸኝነት ህጋዊ ትዳር በሚል እንዲያፀድቅላቸውም ጠይቀዋል። በተጨማሪም የሟቹን ንጉስ 50 በመቶ ሃብት ለማስተዳደር ይፈቀድልኝም ብለዋል።

የዙሉ ባህላዊ ጠቅላይ ሚኒስቴር የሆኑት ልኡል ማንጎሱ ቡቴሌዚ ትናንት ‹‹አሳፋሪ›› ሲሉ ክርክሩን ወደ ፍርድ መሄድ ለደቡብ አፍሪካው ቴሌቪዢን ኤስኤቢሲ ገልፀውታል።

‹‹ገና ከሃዘን ሳትወጣ ባደረገችው በዚህ ተግባር አብዛኛው የንጉሳዊ ቤተብ ተደናግጧል። እነሱ፤ በተለይም የንጉሱ ሚስቶች በዚህ አይነት ሁኔታ ወደ ፍርድ ቤት መሮጣቸው ለንጉሳዊያኑ ቤተሰብ ውርደት ነው›› ሲሉም ለቴሌቪዥን ጣቢያው ገልፀዋል።