ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በፍልቅልቅ ሳቁ የሚታወቀው ስፔናዊ ኮሜዲያን ሞተ

የፎቶው ባለመብት, YOUTUBE
ከሰው ወደ ሰው በሚጋባው ፍልቅልቅ ሳቁ የሚታወቀው ስፔናዊው ኮሜዲያን ሁዋን ጆያ ቦርጃ በ65 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።
'ኤል ሪሲታስ' ወይም ፍልቅልቁ በሚል ቅጽል ስሙ ይታወቅ ነበር።
በርካቶች 'ስፔናዊው ሳቂታ' በሚል በበይነ መረብ ይከታተሉታል።
እአአ 2014 በስፔን ብሔራዊ ጣቢያ ላይ ከታየ በኋላ ነበር ዝናው የናኘው። ኤል ሪሲታስ ሲስቅ የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ወደተለያዩ ቋንቋዎች የተረጎሙም አሉ።
ኮሜድያኑ ረቡዕ እለት ሆስፒታል ውስጥ ሕይወቱ እንዳለፈ መገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።
ባለፈው ዓመትም የጤና እክል ገጥሞት ሆስፒታል ገብቶ ነበር። አንድ እግሩን ካጣ በኋላ ባለፈው ወር አድናቂዎቹ የኤሌክትሪክ መንቀሳቀሻ ሊገዙለት ብር አሰባስበዋል።
ኮሜድያኑ አድናቂዎቹን አመስግኖም ነበር።
ከ20 ዓመት በፊት 'የሱስ ኩዊንትሮ' በተባለ መርሀ ግብር አቅራቢ አማካይነት ቴሌቪዥን ላይ ከቀረበ በኋላ ታዋዊ ሆኗል።
ራቶኔስ ኮሎራስ በተባለው የቴሌቪዥን መሰናዶ ላይ ኮሚዲያኑ ሲቀርብ የአንድ ምግብ አብሳይ ረዳት ሳለ ስለገጠመው ነገር ነበር ያወራው።
ኮሜዲያኑ በአንድ ወቅት 20 ሳሀን ለማፅዳት ሲል ምሽት ላይ ባሕር ውስጥ እንደከተታቸውና በነጋታው ከአንድ ሳሀን ውጪ ሁሉም ውሃ እንደወሰዳቸው ተናግሯል።
ይህን አጋጣሚ ለቴሌቪዥን መርሀ ግብሩ ሲነግረው በጣም ተሳስቀው ነበር።
ንግግሩ ዩቲዩብ ላይ ከተጫነ በኋላ በርካቶች ተመልክተውታል። በተለይም የብዙዎችን ትኩረት የሳበው የኤል ሪሲታስ ሳቅ ነው።
የኮሜድያኑን ሳቅ ከአዶልፍ ሂትለር የመጨረሻው ቀናት እንዲሁም ከሌሎች አጋጣሚዎች ጋር እያጣመሩ በተደጋጋሚ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የጫኑ በርካታ ናቸው።
ሳቁ ከግብጽ ፖለቲካ እና ከአፕል ስልክ ምርቶች ጋር ተያይዞ በሚሊዮኖች ዘንድ ታይቷል።
የኮሜድያኑ ሳቅ እንደ ትዊች ባሉ የጌም ገጾች እና በሌሎችም የበይነ መረብ ገጾች አሁንም ድረስ ዝነኛ ናቸው።












