ከፌስቡክ ጋር ፍጥጫ ውስጥ የገባው አፕል ትርፉ በእጥፍ ጨመረ

የሞባይ የሚመለከት ሰው

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

በቻይና ገበያ ታግዞ የአይፎን ሽያጭ በመጨመሩ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ የአፕል ትርፍ በእጥፍ መጨመሩ ተነገረ።

የአፕል አለቃ ቲም ኩክ ውጤቱን ተከትሎ መጪዎቹ ጊዜያት "ብሩህ ተስፋን" ሰንቀዋል ብለዋል።

ተቀናቃኙ የቴክኖሎጂ ኩባንያው ፌስቡክም ከፍተኛ ገቢ እና ትርፍ አስመዝግቧል።

አፕል በቅርቡ ያስተዋወቀው ሶፍትዌር በዓመቱ መጨረሻ እደርስበታለሁ ብሎ በሚጠብቀው ተስፋው ላይ ውሃ ሊቸልስበት እንደሚችል ፌስቡክ አስታውቋል።

ሸማቾች በበይነ መረብ በመሥራት፣ በመገበያየት እና በመዝናናት ብዙ ጊዜያቸውን በማጥፋታቸው የአፕል ስልኮች፣ መተግበሪያዎች [አፕሊኬሽኖች] እና የሌሎች መገልገያዎች ሽያጩ በወረርሽኙ ወቅትም ቀጥሏል።

ደንበኞች ባለፈው ዓመት ወደ ገበያ የገቡትን የአፕል አዲስ 5 ጂ ስልኮች መግዛት የቀጠሉ ሲሆን ከቤት ለመሥራት እና ለመማር ማክ ኮምፒውተር እና አይፓድ እየገዙኝ ነው ብሏል ኩባንያው።

በእንቅስቃሴ እገዳው ወቅት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እና የሙዚቃ መተግበሪያዎች ሽያጭም እያደገ ነው።

በቻይና የሚደረገው ሽያጭ እጥፍ በሚባል ደረጃ አድጓል። የዚህ ዓመትን የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወሮች ገቢ 89.6 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን ይህም ከአንድ ዓመት በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ከ50 በመቶ በላይ ብልጫ አለው።

ትርፉ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ላይ ከነበረበት 11.3 ቢሊዮን ዶላር ወደ 23.6 ቢሊዮን ዶላር ተመንድጓል።

የፒፒ ፎርሳይት ተንታኝ የሆኑት ፓውሎ ፔስካቶር ይህ ለአፕል "ሌላ ወደ ስኬት የመተኮሻ ሩብ ዓመት" ነው ብለዋል።

አክለውም "አይፎን ለአፕል ዋና የገቢ ምንጭ ሆኖ ይቀጥላል" ሲሉ አክለዋል።

ለሸማቾች ኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች ሳይሆን በማስታወቂያዎች ሽያጭ ገቢ የሚያገኘው ፌስቡክም በመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት ከፍተኛ ገቢ እና ትርፍ አስመዝግቧል።

ሰዎች በቤት ውስጥ ማሳላቸው እና በበይነ መረብ ላይ ያላቸው ቆይታ መጨመር ገቢው 26.17 ቢሊዮን ዶላር እንዲደርስ በማገዝ ከተንታኞች ግምት ከፍ ያለ ገቢ አግኝቷል። ትርፉም ከሚጠበቀው 9.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ነው።

ፌስቡክ በሚቀጥሉት ወራቶች ገቢው የተረጋጋ ወይም በመጠኑ ያድጋል ብሎ እንደሚጠብቅ ግምቱን አስቀምጧል።

በአፕል ይፋ ባደረገው አዲስ አሠራር መሠረት ተጠቃሚዎች መረጃዎቻቸው በመተግበሪያዎች እንዳይሰበሰብ የሚያደርግ አማራጭ በመጀመሩ ሥራውን "በከፍተኛ ሁኔታ" ሊጎዳ ይችላል ሲል አስታውቋል።