ብሪትኒ ስፒርስ የአባቷን ቁጥጥር በተመለከተ ለፍርድ ቤት 'የምናገረው አለ' አለች

ብሪትኒ ስፒርስ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

ብሪትኒ ስፒርስ በግልና በገንዘብ ጉዳዮቿ ዙርያ አባቷ የበላይ ተቆጣጣሪ መሆናቸውን በተመለከተ ከፍርድ ቤት ጋር በቀጥታ ለመነጋገር ጥያቄ እንዳቀረበች ጠበቃዋ ገለጹ።

የታዋቂዋ ድምጻዊት ብሪትኒ አባት ጄሚ ስፒርስ፤ የብሪትኒን የግል እንዲሁም ገንዘብ ነክ ጉዳዮችን በበላይ ተቆጣጣሪነት እንዲመሩ ፍርድ ቤት የወሰነው እአአ በ2008 ነው።

ድምጻዊቷ ከአዕምሮ ጤና ጋር በተያያዘ ሆስፒታል መግባቷን ተከትሎ ነበር ፍርድ ቤት ኃላፊነቱን ለአባቷ የሰጠው።

ጉዳዩን በተመለከተ በዚህ ዓመት ለዕይታ የቀረበ ዘጋቢ ፊልም ውሳኔው ላይ ጥያቄን አጭሯል።

የብሪትኒ ጠበቃ ሳሙኤል ኢንግሀም "ደንበኛዬ ከፍርድ ቤቱ ጋር በቀጥታ ለመነጋገር ጠይቃለች" ብለዋል። ፍርድ ቤቱም ለሰኔ 23 ቀጥሯቸዋል።

ብሪትኒ በአካል ስለመገኘቷና ከተገኘችም ለፍርድ ቤቱ ምን እንደምትናገር አልታወቀም።

አባቷ የግል ሕይወቷን እንዲቆጣጠሩ እንደማትፈልግ ከዚህ ቀደም በጠበቆቿ በኩል አሳውቃለች።

ስምምነቱ ምን ነበር?

የብሪትኒ አባት የልጃቸውን ጉዳዮች በጊዜያዊነት በበላይ ጠባቂነት እንዲመሩ የተወሰነው የብሪትኒን ሆስፒታል መግባት ተከትሎ ነው።

በወቅቱ ብሪትኒ በአዕምሮ ህመም ምክንያት ህክምና ላይ ነበረች። የፍርድ ቤቱ ዝርዝር ውሳኔ ለሕዝብ ይፋ አልተደረገም።

የመርሳት ወይም ሌላ የአዕምሮ ህመም የገጠማቸው ሰዎች ጉዳያቸውን የሚከታተል ሰው በፍርድ ቤት ይወሰንላቸዋል።

ብሪትኒን በተመለከተ ፍርድ ቤቱ ያሳለፈው ውሳኔ በሁለት ይከፈላል። አንደኛው ገንዘብ ነክ ጉዳዮችን የተመለከተ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የግል ጉዳዮቿ ላይ ያተኩራል።

አባቷ የበላይ ተቆጣጣሪ የተደረጉት በሁለቱም ጉዳዮች ነበር። ከዚያ ግን እአአ 2019 ላይ ከጤና ጋር በተያያዘ ምክንያት የግል ጉዳዮቿን መቆጣጠር አቁመዋል።

በአባቷ ምትክ ጆዲ ሞንትጎምሪ የተባሉ እክብካቤ ሰጪ ተተክተዋል። እንክብካቤ ሰጪው በግዜያዊነት ቢቀጠሩም ብሪትኒ ቋሚ ይሁኑልኝ ብላለች።

የ39 ዓመቷ ድምጻዊ ጠበቃ እንደሚናገሩት፤ ብሪትኒ አባቷን ስለምትፈራቸው በግል ጉዳዮቿ የበላይ ተቆጣጣሪ ሆነው ከዘለቁ ወደ ሙዚቃ መድረክ መመለስ አትፈልግም።

የብሪትኒ አድናቂዎች ከማንኛውም ተጽዕኖ ነጻ እንድትሆን የሚጠይቅ ቁልፍ ቃላትን በመጠቀም በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ቅስቀሳ እያደረጉ ነው።

'ፍሬሚንግ ብሪትኒ ስፒርስ' የተባለው ዘጋቢ ፊልም ከወጣ በኋላ የፍርድ ቤት ሂደቱ መነጋገሪያ ሆኗል።

ፊልሙ በብሪትኒ ጉዳይ የበላይ ጠባቂ ለመሆን የነበረውን ሂደት ያሳያል።

ዘጋቢ ፊልሙ ከተለቀ በኋላ ብሪትኒ "በፊልሙ ምክንያት ሁለት ሳምንት አልቅሻለሁ" ብላ በኢንስታግራም ገጿ ጽፋ ነበር።

የብሪትኒ አባት ጠበቃ ቪቭያን ቶረን "እጅግ ልጁን የሚወድ ታማኝ አባት" ሲሉ ነው ደንበኛቸውን የሚገልጹት።

አባትየው የብሪትኒ ጥሪት እንዳይበዘበዝ ማድረጋቸውንም ጠበቃዋ አክለዋል።

የብሪትኒ አባት በልጃቸው የገንዘብ ነክ ጉዳዮች የበለጠ ኃላፊነት እንዲሰጣቸው የካቲት ላይ ፍርድ ቤት ቢጠይቁም ውድቅ ተደርጓል።

አባትየው የብሪትኒን ገንዘብ የሚቆጣጠሩት ቤስመር ትረስት ከተባለ የገንዘብ ተቋም ጋር በጥምረት ነው።