ቼልሲ የሲቲን አራት ዋንጫ የመብላት ተስፋ አጨለመ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የተነቃቃው የቶማስ ቱኽል ቼልሲ የፔፕ ጉዋርዲዮላን አራት ዋንጫ የመብላት ህልም አጨልሟል።
በኤፍ ኤ ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ የተገናኙት ቼልሲና ማንቸስተር ሲቲ በግዙፉ የእንግሊዙ ዌምብሌይ ስታድዬም ቅዳሜ ምሽት ተፋልመዋል።
በጨዋታው ቼልሲ ሞሮኳዊው ሐኪም ዚዬች ባስቆጠራት ብቸኛ ጎል በማሸነፍ ሲቲን ጥለው ለፍፃሜ አልፈዋል።
የቢቢሲ ስፖርት ተንታኞች የማንቸስተር ሲቲው ፔፕ ጉዋርዲዬላ በቶማስ ቱኽል በታክቲክ ተበልጠው ነበር ይላሉ።
ጉዋርዲዮላ በቅዳሜ ምሽቱ ጨዋታ የተለመደውን ዋናውን ቡድናቸውን ይዘው አይደለም የገቡት።
ሲቲ በሚቀጥሉት 11 ቀናት የፕሪሚዬር ሊግ፣ ካራባዎ ዋንጫ እንዲሁም የቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎችን ያደርጋል።
ፔፕ የተወሰኑ ተጨዋቾችን አስቀርተው ወደ ሜዳ የገቡት ይሄን የጨዋታ መደራረብ አስበው ይሆናል ይላሉ ኳስ አዋቂዎቹ።
የቀድሞው የቶተንሃምና ኒውካስትል ተጫዋች ጄርሜይን ጄናስ ሲቲ በዚህ ጨዋታ እንዲሸነፍ አስተዋፅዖ ያደረጉ በርካታ ለውጦች ነበሩ ይላል።
"ፊት ለፊት የተሰለፉት ሶስቱ አጥቂዎች ምንም ሚና አልነበራቸውም። ጉዋርዲዮላ አለኝ የሚለውን ቡድን ይዞ አለመግባቱ አስገርሞኛል" ይላል ጄናስ።
ሲቲዎች በቼልሲ ተረትተው ከኤፍ ኤ ዋንጫ ከመሰናበታቸው ሶስት ቀናት በፊት ቦሩሲያ ዶርትሙንድን በመርታት በጉዋርዲዮላ ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ግማሽ ፍፃሜ አልፈዋል።
ነገር ግን በቅዳሜው የግማሽ ፍፃሜ ፍልሚያ ሲቲዎች አብዛኛውን ጊዜ ቅርፅ አልባ ሆነው ተስተውለዋል።
የቀድሞው የሲቲ ተከላካይ ሚካህ ሪካርድስ ጉዋርዲዮላ ስምንት ተጫዋቾችን ቀይረው መግባታቸው ትክክል አልነበረም ይላል።
የቼልሲው ቶማስ ቱኽል ታክቲክም ሊደነቅ የሚገባው ነው ይላሉ ተንታኞቹ።
በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት ቼልሲ የያዘው ቱኽል ጆዜ ሞውሪንሆን፣ ዩርገን ክሎፕን፣ ካርሎ አንቸሎቲንና አሁን ደግሞ ፔፕ ጉዋርዲዮላን መርታት ችሏል።
ሲቲ በዚህ ዓመት አራት ዋንጫዎችን ማለትም ፕሪሚዬር ሊግ፣ ቻምፒዬንስ ሊግ፣ ኤፍ ኤ ዋንጫ፣ እንዲሁም ካርሊንግ ዋንጫ ለመብላት የነበረው ተስፋ ጨልሟል።
ነገር ግን የፔፕ ጉዋርዲዬላው ሲቲት የቀሩትን ሶስት ዋንጫዎችን ለማንሳት የሚያደርገው ትግል እንደሚቀጥል ይታመናል።
ሲቲ በካርሊንግ ዋንጫ ፍፃሜ ከቶተንሃም ጋር ይፋለማል። በፕሪሚዬር ሊጉ ደግሞ ቀላል የማይባል ግጥሚያ ከአስተን ቪላ ጋር ይጠብቀዋል። አልፎም በቻምፒዬንስ ሊግ ከፒኤስጂ ጋር ይጫወታል።












