ቻይናና አሜሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስን ለመፍታት በጋራ እንደሚሰሩ ገለጹ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሁለቱ ኃያላን አገራት ቻይናና አሜሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተለውን አሉታዊ ተፅእኖ ለመግታት በጋራ ለመስራት ተስማሙ።
የቻይና የአየር ንብረት ልዑክ ሺ ዜኑዋና የአሜሪካ ኣቻቸው ጆን ኬሪ በባለፈው ሳምንት ሻንግሃይ ላይ ተከታታይ ስብሰባን ካደረጉም በኋላ ነው እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት።
አገራቱ ወደ ከባቢ አየር የሚለቋቸውን አማቂ ጋዞችን መጠን ለመቀነስ መስማማታቸውን በጋራ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
በዚህ ሳምንት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በበይነ መረብ የአየር ንብረት ለውጥ ላይ ያተኮረ ጉባኤ እያካሄዱ ሲሆን ቻይናም ይህንን እንደምትጠብቀው አስታውቃለች።
የአለም መሪዎች ይሳተፉበታል ተብሎ በሚጠበቀው ይሄ ጉባኤ የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ዢንፒንግም የመሳተፋቸው ሁኔታ አልተረጋገጠም።
"በአለም ላይ የአየር ንብረት ለውጥ እያስከሰተ ያለው ቀውስ ከፍተኛና አጣዳፊ ምላሽ የሚያስፈልገው እንደ መሆኑ መጠን አሜሪካና ቻይና በጥምረት ይሄንን ለመግታት አብረው ይሰራሉ" በማለት መግለጫው አትቷል።
መግለጫው አክሎም ሁለቱ አገራት ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቁ ጋዞችን እንዴት መቀነስ ይቻላል የሚለውና በፓሪስ ስምምነት መሰረት ሊኖረው የሚገባውን የአለም የሙቀት መጠን ደረጃ ለመድረስ የሚያከናውኗቸውን ተግባራት አብረው ይነድፋሉ ተብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ አገራቱ አዳጊ አገራት ወደ ዝቅተኛ የካርበን ኃይል አጠቃቀም እንዲቀየሩ ለማድረግ የገንዘብ እርዳታ እንደሚለግሱም ተስማምተዋል።
ግሪንፒስ ለተሰኘው የአካባቢ ጥበቃ ቡደን ዋነኛ የአየር ንብረት ለውጥ አማካሪ ሊሹዎ እንዳሉት መግለጫው አዎንታዊ ይዘት ያለው ነው።
"በአየር ንብረት ለውጥን ቀውስ ለመፍታት ሁለቱ አገራት አብረው ለመስራት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ትልቅ መልእክት አለው። ከሻንግሃይ ስብሰባ በፊት ይሄንን ማሰብ አይቻልም ነበር" በማለት አማካሪው ለሮይተርስ ተናግረዋል።
የባይደን አስተዳደር ስልጣን ከተረከበ በኋላ ከፍተኛ የባለስልጣን ልዑካን ቻይናን ሲጎበኙ የሻንግሃዩ የመጀመሪያ ነው። ነገር ግን የአሜሪካና የቻይና ባለስልጣናት ባለፈው ወር በአላስካ ተገናኝተው ነበር።
ከሻንግሃይ ጉዟቸው በፊት ጆን ኬሪ ለሲኤንኤን እንደተናገሩት የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስን ለመግታት የሁለቱ አገራት ትብብር አስፈላጊነትን ነው።
"ልክ ነው በርካታ ቁልፍ በሚባሉ ጉዳዮች ላይ ከቻይና ጋር አንስማማም። ነገር ግን የአየር ንብረት ለውጥ በራሱ የሚቆም ጉዳይ ነው" ብለዋል።












