ኪም ካርዳሺያን እና ካንያ ዌስት ከፍቺ በኋላ ልጆቻቸውን በጋራ ለማሳደግ ተስማሙ

ኪም ካርዳሺያን እና ካንያ ዌስት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ካንዬ ዌስት ከኪም ካርዳሺያን ያፈራቸውን አራት ልጆቹን በስምምነት ለማሳደግ ተስማማ።

ይህ የተሰማው ካርዳሺያን ሰባት ዓመት ከቆየችበት ትዳር እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር የካቲት 19/2021 ፍቺ ለመፈፀም የሚያስችላትን ፋይል መክፈቷን ተከትሎ ነው።

አሜሪካዊው ራፐር ካንዬ እና የቴሌቪዥን እውናዊ ትርዒት ኮከቧ ኪም ካርዳሺያን ትዳራቸውን ለማፍረስ እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል።

ካንዬ ዌስት እና ካርዳሺያን ሁለት ኖርዝ እና ቺካጎ የተሰኙ የሰባት እና ሦስት ዓመት ሴት ልጆች፣ ሴይንት እና ሳላም የሚባሉ የአምስት ዓመት እና የሁለት ወር ወንድ ልጆችን አፍርተዋል።

ካርዳሺያን ለችሎቱ እንዳስገባችው አቤቱታ ከሆነ ሁለቱም ጥንዶች ትዳራቸውን ከመመስረታቸው በፊት በገቡት ስምምነት መሰረት ሀብታቸውን ለይተው ሲኖሩ ነበር።

ጥንዶቹ በየተሰማሩበት ዘርፍ ዝናን ያተረፉ ሲሆን ትዳራቸውም አድናቂዎቻቸው በቅርበት የሚከታተሉት ነበር።

የአርባ ዓመቷ ካርዳሺያን ዝናን ያተረፈችው እኤአ በ2007 እርሷና ቤተሰቧ ላይ የሚያተኩር 'ኪፒንግ አፕ ዊዝ ካርዳሺያን' የተሰኘ የቴሌቪዥን እውናዊ ትርዒት ላይ መቅረብ ከጀመረች በኋላ ነው።

ትርዒቱ በተከታታዮች ዘንድ ከፍተኛ ዝናን ያተረፈ ሲሆን፣ የመጨረሻው ምዕራፍ የሚቀጥለው ዓመት እንደሚቀርብ ታውቋል።

ትዕይንቱ በ14 ዓመታት ቆይታው ኪምና ቤተሰቧን በከፍተኛ ሁኔታ አበልጽጓል። ዓለም እንዲያውቃቸውም አድርጓል።

ኪም ካርዳሺያን እና ካንያ ዌስት በትዳር ለሰባት ዓመት ያህል ቆይተዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኪም ካርዳሺያን ባለፈው ሳምንት በርካታ ሚሊዮን ዶላሮች የሚያንቀሳቅሱ ሁለት ድርጅቶቿ ከቢሊየነሮች ተርታ አሰልፈዋታል።

የ43 ዓመቱ ዌስት፣ በራፕ ሙዚቃ ስምና ዝናን ያተረፈ ሲሆን፣ በፋሽን ዲዛይነርነትም ይታወቃል።

ዌስት ባለፈው ዓመት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ለመሆን በግሉ የተወዳደረ ቢሆንም ሳይሳካለት ቀርቷል።