ኪም ካርዳሺያን እና ባለቤቷ ካንዬ ዌስት ፊርማቸውን ሊቀዱ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኪም ካርዳሺያን ከባለቤቷ ካንዬ ዌስት ጋር ፊርማዋን ልትቀድ እንደሆነ የአሜሪካ መገናኛ ብዙኀን እየዘገቡ ነው።
ራፐሩ ካንዬ ዌስትና ኪም ካርዳሺያንስ ላለፉት ሰባት ዓመታት በትዳር ተጣምረው የኖሩ ሲሆን አራት ልጆችንም አፍርተዋል።
ሰማንያቸውን ሊቀዱ ነው፣ እህል ውሃቸው አብቅቷል የሚል ወሬ ለበርካታ ወራት ሲናፈስ ከቆየ በኋላ ቲኤምዚ የተሰኘው የታዋቂ ሰዎችን ጉዳይ የሚዘግበው ድረ ገጽ እውነት ነው ሲል ተናግሯል ።
እንደ አሜሪካ መገናኛ ብዙኀን ከሆነ የ40 ዓመቷ ኪም ካርዳሺያን፣ በጋራ ያፈሯቸውን ልጆች በጋራ ለማሳደግ እንዲችሉ መጠየቋ የተዘገበ ሲሆን ጥንዶቹ ግን በጉዳዩ ላይ በይፋ አስተያየት አልሰጡም።
ኪም ካርዳሺያንም ሆነች ካንዬ ዌስት በየግላቸው እጅግ በጣም ዝነኛ እና ስኬታማ ናቸው።
ኪም ለመጀመሪያ ጊዜ ዝናን በእጇ ያስገባችው በ2007 በ E! ቴሌቪዥን ጣብያ ኪፒንግ አፕ ዊዝ ዘ ካርዳሺያንስ በተሰኘው የቤተሰቧን የእለት ተዕለት እንቅስቃሴን በሚያሳየው እውናዊ ተከታታይ የቴሌቪዥን ትርዒት ላይ ነው።
ይህ እውናዊ የቴሌቪዥን ትርዒት ከተጀመረ ጀምሮ በተመልካች ዘንድ በጣም ዝነኛ ሲሆን 21ኛው እና የመጨረሻው ክፍል በሚቀጥለው ዓመት ይተላለፋል ተብሎ እቅድ ተይዞለታል።
ኪም ካርዳሺያን ከቴሌቪዥን ትርዒቱ ባሻገር በሌሎች የንግድ መስኮችም እድል ፊቷን ያበራችላት ሴት ናት።
ከሞባይል መተግበሪያ እስከ መዋቢያ ምርቶች ንግድ ውስጥ የተሰማራቸው ኪም ካርዳሺያንስ በፎርብስ የሃብታሞች ዝርዝር ውስጥ ሃብቷ 780 ሚሊዮን ዶላር መድረሱ ተመዝግቧል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ካንዬም ቢሆን ላለፉት 15 ዓመታት በራፕ ሙዚቃ ውስጥ ስሙን የተከለ ድምጻዊ ነው።
ይህ የግራሚ ሽልማት አሸናፊ የሆነው ራፐር፣ በፋሽኑም መስክ የስኬት ፀሀይ ወጥቶለታል።
ጥንዶቹ ከመጋባታቸው በፊት ለረዥም ጊዜ ጓደኛሞች የነበሩ ሲሆን ካንዬ ዌስት ለመጀመሪያ ጊዜ በቤተሰቡ እውናዊ የቴሌቪዥን ትርዒት ላይ በ2010 ቀርቧል።
የጥንዶቹ የመጀመሪያ ልጅ ኖርዝ የምትባል ስትሆን እኤአ በ2013 ሰኔ ወር ላይ ነው የተወለደችው።
ካንዬ ልጃቸው በተወለደችበት ዓመት ለኪም ካርዳሺያን የታገቢኛለሽ ጥያቄ ሲያቀርብ የሳን ፍራንሲስኮን ግዙፍ ስታዲያም ተከራይቶ፣ ኦርኬስትራ አደራጅቶ፣ ቤተሰቦቿ እና የቴሌቪዥን ፕሮግራሙ ካሜራ ባለሙያዎች በተገኙበት ነበር።
በ2014 በጣሊያን ጋብቻቸውን የፈፀሙት ጥንዶቹ ሲሳሳሙ የተነሱትን ምስል በኢንስታግራም ላይ አጋርተውት በማህበራዊ ድረ ገፁ ታሪክ እጅጉን የተወደደ ምስል ተብሎ ተመዝግቧል።
ከዚህ በኋላ ኪምና እህቷ የማህበራዊ ሚዲያን ተከታዮቻቸውን ተጠቅመው ወደ ስኬታማ የንግድ ስራ አምርተዋል።
በሚቀጥለው ዓመት ኪም ወንድ ልጅ፣ ሴይንት ዌስት፣ ወልዳለች። ከዚያ በመቀጠልም ቺካጎ እና ፕስላም የተሰኙ ልጆችን አፍርተዋል።
በ2016 ኪም ካርዳሺያን በፈረንሳይ ባረፈችበት ሆቴል ውስጥ ክትትል ሲያደርጉባት በነበሩ ሰዎች ዘረፋ ተፈጽሞባታል።
ከዚያም በኋላ ባለፈው ዓመት ካንዬ ዌስት በአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ እጩ ሆኖ ተሳትፏል።
ለበርካታ ወራት የጥንዶቹ የፍቺ ወሬ ሲናፈስ ቆይቶ ኪም ካርዳሺያን በፍቺ ዙሪያ ጥርሷን የነቀለች ጠበቃ፣ ላውራ ዋሴር፣ መቅጠሯ ተሰምቷል።
ይህ ጽሑፍ በInstagram. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የInstagram ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ Instagram ይዘት መጨረሻ












