ሰባት ኬንያውያን የእርሻ ሰራተኞች ዓለማቀፉን ድርጅት በስኮትላንድ ከሰሱት

ሻይ ቅጠል የምትለቅም ግለሰብ
ታትሟል

ሰባት ኬንያውያን የሻይቅጠል ማሳ ሰራተኞች በስራ ላይ ለደረሰባቸው ጉዳት የዓለማችን ትልልቅ የሻይ አምራች ኩባንያን ስኮትላንድ ውስጥ ከሰዋል።

የሻይ ቅጠሎችን በመሰብሰብ የሚተዳደሩት ሰባቱ ኬንያውያን እንደሚሉት በስራ ቦታቸው ላይ ምቹ ባልሆነ የስራ ሁኔታ ምከንያት ከፍተኛ የጤና ችግር ደርሶባቸዋል።

የሻይ ማሳዎቹን በባለቤትነት የሚያስተዳድረው 'ጄምስ ፊንሌይ' የተባለው ዓለማቀፍ ድርጅት ነው።

ድርጅቱ የቀረበበትን ክስ ያጣጣለ ሲሆን በስራ ቦታዎች ላይም ቢሆን ምንም አይነት የጤናና የደህንነት ችግር እንደሌለ ገልጿል።

ጄምስ ፊንሌይ በአውሮፓውያኑ 1750 ጥጥ በመነገድ ላይ የተመሰረት ሲሆን በአምስት አህጉራት ቅርንጫፎች አሉት። ታዋቂው ስታርባክስ ጭምር ከደንበኞቹ ዝርዝር ውስጥ አለ።

ድርጅቱ የሚያመርተው የሻይ ቅጠል መላው ዩናይትድ ኪንግደምን ይደርሳል። ምንም እንኳን ከ15 ዓመታት በፊት ዋና መቀመጫውን ከስኮትላንድ ግላስኮው ወደ ለንደን ቢያዞርም የንግድ ፈቃዱ የተመዘገበው ግን ስኮትላንድ አበርደን ውስጥ በመሆኑ ክስ የተመሰረበትም እዚያው ነው።

ሰባቱ ኬንያውያን ሴቶችና ወንዶች ኤደንብራ ውስጥ ለሚገኘው ፍርድ ቤት ባቀረቡት ክስ መሰረት በስራ ቦታቸው ላይ ለደረሰባቸው የጤና እክል ለእያንዳንዳቸው 15 ሺ ፓውንድ ካሳ እንዲከፈላቸው ጠይቀዋል።

የሰራተኞቹ አስተባበሪ አይዛክ ኦኬሮ እንደሚለው በስራ ቦታ ላይ በርካታ የጤና እክሎች ያጋጠማቸው ሲሆን የጀርባ አጥንታቸውም ላይ ጉዳት ደርሷል።

ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ ''የሻይ ማሳው ሰራተኞች እንደሚሉት ላለፉት ዓመታት ድርጅቱን ሲያገለግሉ በቆዩባቸው ዓመታት በጊዜ ብዛት ከባድ የጤና ችግር ውስጥ ገብተዋል። ይህ ደግሞ ህይወታቸውን በእጅጉ ጎድቶታል'' ብሏል።

''ጉዳቶቹ አካላዊና ስነልቦናዊ ናቸው''

አይዛክ እንደሚለው የክስ ሂደቱ ሲጀመር በርካታ ሰራተኞች በድርጅቱ ውስጥ የነበሩ ሲሆን በአሁኑ ሰአት ግን በስራ ላይ ያለው አንድ ግለሰብ ብቻ ነው። ሌሎች ሰራተኞች በስራቸው መቀጠል ስላልቻሉ ለቀዋል አልያም ጡረታ እንዲወጡ ተገደዋል።

ይህ የክስ ሂደት በርካታ ነገሮችን ሊቀይር እንደሚችል አይዛክ ያምናል።

'' ድርጅቱ ሰራተኞቹ ያሉበትን የስራ ቦታ ሁኔታ እንዲመለከትና ለውጥ እንዲያደርግ ይህ ክስ ያስገድደዋል ብዬ አስባለሁ። ይህ አሁንም በተመሳሳይሁኔታ የሻይ ቅጠሎችን በመሰብሰብ ለሚተዳደሩ ሰራተኞች ተስፋ የሚሰጥና ነገሮችን ሊቀይር የሚችል ነው። ኬንያውያን ሰራተኞች እነዚህ ሰባቱ ሰራተኞች የደረሰባቸው አይነት ህመም እንዳያጋጥማቸው ይረዳል'' ብሏል።

የጄምስ ፊንሌይ ዋና ዳይሬክተር ጋይ ቻምበርስ በበኩላቸው ''እኛ በሁሉም ነገር ፍጹም እንዳልሆንን እናውቃለን። ምናልባት ማሻሻል የሚገቡ በርካታ ነገሮች እንዳሉም እናውቃለን። ነገር ግን እኛን የሚተቹን ሰዎች የአካባቢውውን ማህበረሰብ ለመጥቀም የምንሰራውን ስራ በደንብ አያስተውሉትም'' ብለዋል።

ድርጅቱ እንደሚለው ኬንያ ውስት በኪሪቾ እና ቦሜት በሚገኙት የሻይ ማሳዎቹ ውስጥ እስከ 8 ሺ የሚደርሱ ሰዎች በቀጥታ የስራ እድል የተፈጠረላቸው ሲሆን ለአካባቢው ቀላል የማይባል ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።

በመግለጫው አክሎም '' በስራ ቦታ ላይ ከፍተኛውን የደህንነት መመሪኣ ለመተግበርና ሰራተኞቻችን ጤንነታቸው እንዲጠበቅ ለማድረግ ነው ዋነኛ ዓለማችን'' ብሏል።