የዓለም ዋንጫ በሻኪራ ዜማ፣ በዳንስ እና በተቃውሞ ታጅቦ በሜክሲኮ ተጀመረ

የ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የ2026ቱ የዓለም ዋንጫ በደማቅ ቀለሞች በተሞላ የማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ በዳንስ እና በዓለም የሙዚቃ ፈርጧ ሻኪራ የሙዚቃ ዝግጅት በሜክሲኮ ከተማ ተጀመረ።

በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎች በ40 ዓመታት ውስጥ በአገራቸው የተሰናዳውን የዓለም ዋንጫ ለመከታተል በሜክሲኮ ከተማ በሚገኘው በዝነኛው አዝታካ ስታዲየም ታድመዋል።

ነገር ግን ከስታዲየሙ ውጭ አክራሪ ተቃዋሚዎች ሁነቱን ለማስተጓጎል ግጭት ሲጀምሩ በፀጥታ ኃይሎች ከባድ ምላሽ ተሰጥቷቸዋል።

በአብዛኛው ክፍሉ እግር ኳስ ዋነኛ የሁነቱ ማጠንጠኛ የነበረ ሲሆን፤ ሜክሲኮ ደቡብ አፍሪካን ሁለት ለዜሮ ማሸነፏ ተከትሎ ትልቅ ፈንጠዚያ ታይቷል።

ከቤተሰቦቹ ጋር የመክፈቻ መርሃ ግብሩን ለመታደም የመጣው ሀቪየር ፕሬዝ ደስታው እዚህ ለመድረስ ካጋጠሙ ችግሮች እንደሚያመዝንበት ለቢቢሲ ተናግሯል።

ሻኪራ በዓለም ዋንጫ ማስጀመሪያ ላይ ከሌሎች ዳንሰኞች ጋር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ዝነኛዋ ሻኪራ በሜክሲኮ ከተማ በተደረገው የዓለም ዋንጫ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ ሙዚቃዋን አቅርባለች

"ቲኬት በማግኘታችን ደስተኞች ነበርን እና ይህ ልዩ አጋጣሚ ነው። ከዚህ በፊት ዓለም ዋንጫን ተመልክቼ ስለማላውቅ ቤተሰቦቼን ማምጣቴ ድንቅ ነው" ብሏል።

"ሜክሲኮ ትክክለኛው መስመር ላይ እንድትሆን ነው የምፈልገው፤ ዛሬ አሸንፋ ጎሎችን እንድታስመዘግብ። እናም ከዚህ በኋላ የት ድረስ እንደምንሄድ እናያለን።"

82 ሺህ ሰዎችን በሚይዘው ስታዲየም ጠንካራ የደኅንነት ቁጥጥር የነበረ ቢሆንም በፖሊስ እና በተቃዋሚዎች መካከል የተከሰተው ግጭት በአቅራቢያው የነበረውን የባቡር ጣቢያ በጊዜያዊነት እንዲዘጋ አድርጓል።

የሜክሲኮ ባለሥልጣናት 800 ከሚሆኑ ተቃዋሚዎች ውስጥ 200 የሚጠጉ ጭንብል ያጠለቁ ግለሰቦች በሁለት ቡድን በመሆን ከሕግ አስከባሪዎች ጋር እንደተጋጩ ገልፀው፤ ሁኔታውን ፖሊስ "ወዲያው በቁጥጥር ስር አውሎታል" ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በሜክሲኮ የአደንዛዥ እፅ ጦርነት የት እንደገቡ ያልታወቁ ሰዎች ቤተሰቦች እና መምህራን የተለያዩ የተቃውሞ ሰልፎችን በማድረግ፤ ጥያቄዎቻቸውን ለማጉላት አገሪቱ በመላው ዓለም ዓይን ውስጥ መግባቷን ተጠቅመዋል።

ሜክሲኮ የ2026ቱን የዓለም ዋንጫ ከአሜሪካ እና ካናዳ ጋር የጋራ አዘጋጅ ናት።

ከጨዋታው አስቀድሞ ደጋፊዎች በሻኪራ፣ ኮሎምቢያዊዊ ጄ ባልቪን፣ በአፍሮቢት አቀንቃኙ በርና ቦይ እና በላቲን የሙዚቃ ኮከብ ዳኒ ኦሽን የሙዚቃ ዝግጅት ታድመዋል።

የሜክሲኮ ሙዚቀው ፋህር ኦልቬራ ታዋቂውን 'ኦይ ሚ አሞር' የተሰኘውን ሙዚቃ ለማዜምም መድረኩን ተረክቧል።

የዓለም ዋንጫ መጀመሩን ለማብሰር "ቤቪኒዳ ሜሂኮ፤ እንኳን ወደ ሜክሲኮ በሰላም መጣችሁ" በማለት አንድ ሙዚቀኛ በይፋ አውጇል።

"የብዝኃነት፣ የታሪክ እና የኩራት አገር ነን፤ እግር ኳስ ትውልዶችን በማስተሳሰር የልብ ትርታን ይይዛል" ብሏል።

ትርኢት አቅራቢዎች የነባር ሕዝቦችን አልባሳት ለብሰው

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ትርኢት አቅራቢዎች የነባር ሕዝቦችን አልባሳት ለብሰው

ትርኢት አቅራቢዎች የነባር ሕዝቦችን አልባሳት ሲለብሱ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ወርቃማ አልባሳትን በመልበስ በራሳቸው ላይ ግዙፍ ወርቃማ ኳስ አድርገው ታይተዋል።

በሰዎች የተሞላው ስታዲየም አብዛኞቹ የአገራቸውን ሜክሲኮ ብሔራዊ ቡድን መለያ ቀለሞች ለብሰው ነበር።

የዘንድሮውን የዓለም ዋንጫ ይፋዊ ዝማሪ 'ዲኤንኤ' የኦፔራ ኮከቡ አንድሪያ ቦቻሌ እና የኬ-ፓፕ ድምፃዊው ኢጃይ አቅርበዋል።

የደቡብ አፍሪካን ብሔራዊ የሕዝብ መዝሙር የግራሚ አሸናፊዋ ታይላ ስትዘምር፤ የሜክሲኮን መዝሙር ደግሞ አሊሃንድሮ ፈርናንዴዝ 80 ሺህ ለሚሆኑ ታዳሚዎች አቅርቧል።

ፊፋ ለማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ዓለም አቀፍ አርቲስቶችን ያሰማራ ሲሆን በርካቶችም 18 ሙዚቃዎችን በያዘው በ2026 የፊፋ ዓለም ዋንጫ አልበም ውስጥ ይገኛሉ።

የሜክሲኮ ደጋፊዎች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የሜክሲኮ ደጋፊዎች