ኤለን መስክ የስፔስኤክስ የአክሲዮን ገበያ በመጨመሩ የዓለማችን የመጀመርያው ትሪሊየነር ሆነ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አርብ ዕለት የኤለን መስክ የኅዋ ኩባንያ ስፔስኤክስ ከፍተኛ የአክሲዮን ሽያጭ ማካሄዱን ተከትሎ የዓለማችን የመጀመርያው ቱጃር ባለ ትሪሊየነር ሆነ።
የቴስላ እና ስፔስኤክስ መሥራች የሆነው መስክ የዓለማችን ቁጥር አንድ ሃብታም የ1.11 ትሪሊየን ባለቤት በመሆን ስሙን ከቱጃሮች አናት ላይ በደማቅ ጽፏል።
ብሉምበርግ የቱጃሮች ዝርዝር ባወጣበት ዘገባው ላይ እንደጠቀሰው ከሆነ መስክ ሃብቱ አንድ ትሪሊየን የሞላለት የሮኬት፣ ቴሌኮሙኑኬሽን እና የሰው ሠራሽ አስተውሎት ኩባንያው በናስዳቅ የአክሲዮን መገበያያ ላይ 2.2 ትሪሊየን ዶላር ካስመዘገበ በኋላ ነው።
ኩባንያው የአክሲዮን ድርሻዎቹ የመሸጫ ዋጋ እያንዳንዳቸው 135 ዶላር የነበሩ ቢሆንም ግብይቱ እንደተጀመረ በ150 ዶላር ሲሸጡ ቆይተው በኋላም ባለሃብቶች በኅዋ ላይ እና ከመስክ ጋር ግንኙነት ባላቸው ንግዶች ላይ ለመሰማራት ያላቸው ፍላጎት በመጨመሩ 176.50 ዶላር ደርሰዋል።
የስፔስ ኤክስ አክሲዮን ሽያጭ ከመዘጋቱ በፊት 161 ዶላር ደርሶ ነበር ተብሏል።
መስክ በስፔስኤክስ ላይ የ42 በመቶ ድርሻ ያለው ሲሆን ይህም በሚያካሄዳቸው እያንዳንዱ ውሳኔዎች ላይ የተናጠል ቁጥጥር ማድረግ እንዲችል ያስችለዋል።
ባለሃብቶች በኩባንያዎቹ ላይ ያፈሰሱትን ገንዘብ ለሚፈልገው ዓላማ ማውጣት ያስችለዋል።
እንደ ብሉምበርግ ከሆነ በስፔስኤክስ ያለው የአክሲዮን ድርሻ 767.1 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም በቴስላ ደግሞ 168 ቢሊዮን ደርሷል።
ከዚህ በተጨማሪ በሁለቱም ላይ በስፔስ ኤክስ እና በቴስላ ወደፊት በሚቀመጠው ዋጋ መግዛት የሚያስችል የ53.8 በመቶ እና የ116.4 ቢሊዮን ድርሻዎች አሉት።
ይህም ወደፊት በሚኖር ግብይት የአክሲዮን ገበያ ዋጋው ከጨመረ የበለጠ አትራፊ ይሆናል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የመስክ የዓለማችን የመጀመርያው ትሪሊየነር መሆን ወዲያውኑ የሃብት ኢፍትሃዊነትን በሚመለከት ክርክር አስነስቷል።
የመስክ ሃብት የፖላንድ ወይንም የስዊትዘርላንድ ምጣኔ ሃብት ከሚያመነጨው አጠቃላይ ገቢ ጋር ተመሳሳይ ነው።
ይህ የዓለማችን ቱጃርን በዓለም ፖለቲካ ላይ ወሳኝ እና ከፋፋይ እንዲሆን ያደርገዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዳግም ለመመረጥ በሚያደርጉት ቅስቀሳ ወቅት የወቅቱን አገሪቱን መሪዎች ተችቶ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ሰጥቷቸዋል።
መስክ ትራምፕን ለድል ከበቁ በኋላ የማራላጎ እና የዋይት ሐውስ ቤተኛ ሆኗል። የመንግሥትን ብቃት ያቀላጥፋል የተባለውን መሥሪያ ቤትንም (ዶጅ) መርቷል።
የመንግሥት ወጪን በከፍተኛ ሁኔታ ቢቀንስም መስክ ለዩኤስአይዲ መዘጋት ምክንያት ነው።
እንዲህ ዓይነት እርምጃዎች እአአ በ2030 ተጨማሪ 14 ሚሊዮን ሞቶች እንዲመዘገቡ አንደሚያደርግ ላንሴት ሜዲካል ጆርናል ላይ የታተመ ጥናት አስጠንቅቋል።
መስክ በዩናይትድ ኪንግደም እንዲሁም ሌሎች አገራት የሚገኙ አመራሮችን ከስደተኞች ጋር በተገናኘ የተቸ ሲሆን የዘር ክፍፍልንም ሲያቀነቅን ተስተውሏል።
መስክ በተደጋጋሚ ከዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በሰጣቸው አስተያየቶች የተነሳ ተቃቅሯል።
የዓለማችን ቱጃርን ሃብት ከተቹ አሜሪካውያን ፖለቲከኞች መካከል በርኒ ሳንደርስ እና ኤሊዛቤት ዋረን ይገኙበታል።
ዋረን ይህ "የማንቂያ ደወል" ሊሆነን ይገባል በማለት የሃብት ታክስ መጣል እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ነገር ግን መስክ ትሪሊየነር መሆኑ የተገለጸው በወረቀት ላይ ብቻ ነው።
ምክንያቱ ደግሞ ሃብቱ በአጠቃላይ የተሳሰረው ከቴስላ እና ከስፔስኤክስ አክሲዮኖች ጋር መሆኑ ነው። የትኛውንም የስፔስኤክስ አክሲዮን ድርሻውን ቢያንስ ለአንድ ዓመት መሸጥ አይችልም።
ስፔስኤክስ አክሲዮኑ ለሽያጭ በይፋ ሲቀርብ ከ4400 በላይ አሁን እየሰሩ ያሉ እና ከዚህ በፊት ተቀጣሪዎች የነበሩ ሰዎች ያተርፋሉ። ይህም የሚሆንበት የአክሲዮን ድርሻዎቹ በክፍያ መልክ የተሰጣቸው በመሆኑ ነው።
ኤሎን አሜሪካዊ የሆነው እአአ በ2002 ነበር።
የስፔስ ኤክስ ድርሻ ዋጋ በብዛት የተመሠረተው ወደፊት ሊኖር ይችላል በሚል የገበያ ተስፋ ላይ ነው።
በአሁኑ ወቅት ኩባንያው በሰው ሠራሽ አስተውሎት ላይ እያወጣ ባለው ገንዘብ የተነሳ አትራፊ አለመሆኑ ተገልጿል። እአአ በ2025 እና 2026 ከ9 ቢሊዮን በላይ ኪሳራ እንዳጋጠመው ለመንግሥት አስታውቋል።
የኩባንያው ዋና ትኩረት ሮኬትን ወደ ኅዋ ለማስወንጨፍ የሚያስችሉ ክፍሎችን ማምረት እና ማስወንጨፍ ነው።
ስፔስኤክስ ከሰው ሠራሽ አስተውሎት በተጨማሪ ስታርሊንክ የኢንተርኔት ሳተላይቶችን ያመርታል።















