የልጁን አንገት ቀልቶ የገደለው ህንዳዊ በቁጥጥር ስር ዋለ

የሴቶችን ጥቃት የሚከላከል አርማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በህንድ የልጁን አንገት ቀልቶ ገድሏል ያለውን አባት በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አስታውቋል።

ክስተቱ የተፈጠረውም በሰሜናዊ ህንድ ኡታር ፕራዴሽ ግዛት መሆኑም ተዘግቧል።

ሳርቬሽ ኩማር የተባለው ግለሰብ የተቆረጠውን የ17 አመቱን ልጅ ጭንቅላት ወደ ፖሊስ ጣቢያም ሲያመራ ነው በቁጥጥር ስር የዋለው።

ፖሊስ የቀረፀው ቪዲዮ እንደሚያሳየው የ17 አመት ሴት ልጁ እሱ ከማይፈልገው ወንድ ጋር ግንኙነት በመፍጠሯ መበሳጨቱን ሲናገር ነበር።

በህንድ ከቤተሰቦቻቸው ውጭ የፍቅር ግንኙነት በመጀመራቸው ወይም በትዳር በመጣመራቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሴቶች በቤተሰብ አባላት ይገደላሉ።

በዚሁ ቪዲዮም ላይ እንደሚታየው ልጁ እሱ ከማይፈልገው ወንድ ጋር ግንኙነት መጀመሯን በቅርብ መረዳቱንና በከፍተኛ ሁኔታ እንዳስቆጣው ነው።

ቤት ውስጥም ብቻዋን እንዳገኛትና መኝታ ክፍሏን ቆልፎ ጭንቅላቷን በስለት እንደቆረጠው ሲናገርም በቪዲዮው ላይ ይሰማል።

ግለሰቡ ጭንቅላቷንም ይዞ በመንገድ ላይ ሲረማመድ ያዩ የአካባቢው ነዋሪዎች ፖሊስ ጠርተዋል።

ግለሰቡም ለፖሊስ እንደተናገረው ቀሪ አካሏንና የገደለበትን ስለት በመኝታ ክፍሏ ውስጥ እንዳስቀመጠውና ለፖሊስ እጁን ለመስጠት "እያቀናሁ ነበር" ብሏል።

ፖሊስ ምርመራ መክፈቱን አስታውቋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ አንድ ፖሊስ የልጅቷን የተቆረጠ ጭንቅላት ባልተገባ መልኩ ይዟል በሚል ከስራ ተባርሯል።

ግድያው የተፈፀመባት ኡታር ፕራዴሽ ግዛት በህንድ ውስጥ በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ደረጃ የአንደኛነት ስፍራን የያዘ መሆኑንም ብሔራዊ የወንጀል ቢሮ አስታውቋል።

ህንድን ጨምሮ በአንዳንድ አገሮች በማህበረሰቡ ዘንድ "አስነዋሪና ክብርን የሚያዋርድ" ስራ ሰርተዋል የሚባሉ ሴቶች "የክብር ግድያ" በሚባለው መንገድ ይሞታሉ።

ቁጥሩ ምን ያህል እንደሆነ በእርግጠኝነት ባይታወቅም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሴቶች "የክብር ግድያ" በሚባለው ሁኔታ ህይወታቸው እንደሚቀጠፍ ይናገራሉ።

በህንድ ይህ ኋላ ቀር ባህል በአሁንም ሰዓት በተለያዩ ማህበረሰቦች ተንሰራፍቶ ይገኛል።

በርካታ ቤተሰቦች ልጆቻቸው ከሚፈቅዱት ሃይማኖትና የመደብ ደረጃ ውጭ የፍቅርም ሆነ የትዳር አጋር ከመሰረቱ የሚገደሉ ሲሆን ይህም በአካባቢው ካስቴ ተብሎ በሚታወቀው የመደብ ምክር ቤት ተፈፃሚ ይሆናል።

የ'ክብር ግድያ' ምንድን ነው?

የክብር ግድያ በቤተሰብ ላይ ውርደትን አስከትለዋል የሚባሉ ሴቶች ላይ በቤተሰብ አባል የሚፈፀም ግድያ ነው።

የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እንዲሁም ሂዩማን ራይትስ ዋች ለግድያው ተብለው ከሚሰጡ ምክንያቶች መካከል ከሰበሰቧቸው መረጃዎች፦

  • ቤተሰብ የመረጠላቸውን ባል አለማግባት
  • ወሲባዊ ጥቃት ወይም መደፈር ሲፈፀምባቸው
  • ከጋብቻ ውጭ ወሲባዊ ግንኙነት ቢኖራቸው ወይም ኖሯቸዋል ተብሎ የሚታመን ከሆነ

ከዚህም በተጨማሪ አለባበሳቸው 'ያልተገባ' ከሆነ፣ 'የማይሆን' ጠባይ ካሳዩ እንዲሁም 'ታዛዥ' ካልሆኑ ግድያው ይፈፀምባቸዋል ተብሏል።

በአውሮፓውያኑ 2012 ጠቅላይ ፍርድ ቤት በ"ክብር ግድያ" የሚወነጀሉ ግለሰቦች በሞት ፍርድ እንዲቀጡ ወስኗል።