ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አንጀሊና ጆሊ የቀድሞው የብሪታኒያ መሪ የሳሉትን ስዕል በ7 ሚሊዮን ዩሮ ሸጠች
የቀድሞው የዩናትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ዊንስተን ቸርችል የሳሉት እና በአንጀሊና ጆሊ እጅ የቆየው ስዕል በለንደን ለጨረታ ቀርቦ በ ሰባት ሚሊዮን ዩሮ ተሸጠ።
ስዕሉ የተሸጠበት ዋጋ ያወጣል ተብሎ ከተገመተው አራት እጥፍ ሆኗል።
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ግዜ የተሳለው እና በማራኬሽ የሚገኘውን የኩቶውቢያ መስጊድ የሚያሳየው ስዕል፤ የገዛው ሰው ማንነቱ አይታወቅም።
የክርስቲስ ቃል አቀባይ እንደገለጹት ‹‹ይህ ስዕል የቸርችል ወሳኝ ስራ ነው፤ በጦርነት ወቅት የሰሩት ብቸኛ ስራቸው ነው››።
ቸርችል ከ ካዛብላንካ ኮንፈረንስ ሲመለሱ ነበር ከሞሮኮዊቷ ከተማ በመነሳት ይህንን የኩቶቢያ መስጊድ ማማዎችን የሚያሳየውን ስዕል የሳሉት።
ከዛም የጦር ሜዳ አጋራቸው ለነበሩት የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ፍራንክሊን ሮዝቬልት በስጦታነት አበርክተውታል። ይህ ስራ በሂደት በኒው ኦርሊያንስ በተደረገ ሽያጭ ነበር በ1993 ዓ.ም ወደ ተዋናይት አንጀሊና ጆሊ እጅ የገባው።
ሰኞ በተካሄደው እና በአብዛኛው በስልክ በተከናወነው ጨረታ ከ1.5 እስክ 2.5 ዩሮ ያወጣል ተብሎ የተገመተው ስዕል የኮሚሽን ክፍያዎች ሲጨመሩ 8.2 ሚሊዮን ብር ማውጣቱ ተገልጿል።
ቸርችል ወደ ፖለቲካ ከመግባታቸው በፊት የጦር ሠራዊት አባል የነበሩ ሲሆን በ40 ዓመታቸው አካባቢ ነው መሳል የጀመሩት። ይህንን ሥራ በሰሩበት ወቅትም አብዛኛው የሞሮኮ ክፍል በፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ስር ነበር።
በማራኬሽ ከተማ ከሚገኘው ቪላ ታይለር በረንዳ ላይ ሆነው ነበር ስዕሉን የሳሉት።
‹‹ይህ እንግዲህ የቸርችል በግለሰብ ደረጃ ያለ እና የጠበቀ የዲፕሎማሲ መንገድ ነው›› ሲሉ በክርሲቲስ የብሪታኒያ ዘመናዊ ስነ ጥበብ እና የአይሪሽ ስዕሎች ባለሙያ የሆኑት ኒክ ኦርቻርድ ይናገራል።
ከዚህ ቀደም ቸርችል ማራኬሽን ለመጀመሪያ ግዜ በጎበኙበት ግዜ የሳሉት ስዕል በ 1.5 ሚሊዮን ዩሮ ነበር የተሸጠው።
የአንጀሊና ጆሊ የቀድሞ ባለቤት ብራድ ፒት የስዕል ስራዎችን ተግቶ ይሰበስብ ነበር። ጥንዶቹ በትዳር ቆይታቸውም ታዋቂ የሆኑ የስዕል ስራዎችን በጋራ ሰብስባዋል።