ጃዋር መሐመድ፡ እነ አቶ ጃዋር ወደ ግል ሆስፒታል ተወሰዱ

ታትሟል

አቶ ጃዋር መሐመድ፣ በቀለ ገርባ እና ሐምዛ አደነ ወደ መረጡት የግል ሆስፒታል ዛሬ ረፋዱ ላይ ተወሰዱ።

ከ30 ቀናት በላይ በረሃብ አድማ ላይ እንደሚገኙ የተነገራለቸው ተከሳሾች፤ የተወሰዱት ላንድማርክ ተብሎ ወደሚጠራው ሆስፒታል መሆኑን ቢቢሲ ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ምንጮች እና የቤሰተብ አባላት መረዳት ችሏል።

ተከሳሾቹ ታሰረው ይገኙበት ከነበረው ቃሊቲ ማረሚያ ቤት በአምቡላንስ ተጭነው በጸጥታ ኃይሎች ታጅበው ወደ ሆስፒታሉ ተወሰደዋል።

የቤተሰብ አባላት እና ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጭ እንደሚሉት፤ የተከሳሽ ቤተሰብ አባላት ወደ ሆስፒታሉ እንዳይገቡ መከልከላቸውን እና ተከሳሾቹ ስለሚገኙበት የጤና ሁኔታ ማወቅ እንዳልተቻለ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ተከሳሾቹ ከግል ሃኪሞቻቸው ጋር እንደሚገኙ የቤተሰብ አባላቱ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

በሆስፒታሉ ዙሪያም በርካታ የጸጥታ አካላት ተሰማርተው እንደሚገኙ ምንጮቹ ተናግረዋል።

የተከሳሽ ጠበቆች እና የቤተሰብ አባላት እንደሚሉት ከሆነ፤ ጃዋር መሐመድ፣ በቀለ ገርባ፣ ደጀኔ ጣፋ እና ሐምዛ አዳነ የረሃብ አድማ ማድረግ ከጀመሩ ዛሬ 34ኛ ቀናቸው ላይ ይገኛሉ።

ተከሳሾቹ የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ፣ በፖለቲከኞች ላይ የሚደርሰው ወከባ ይቁም እንዲሁም የቤተሰብ አባላት ችሎት እና ማረሚያ ቤት ለጥየቃ ሲመጡ የሚደርስባቸው ወከባ ይቁም በማለት የረሃብ አድማውን እያደረጉ እንደሆነ ጠበቆቻቸው ይናገራሉ።

ተከሳሾች እንዴት ወደመረጡት ሆስፒታል ሊወሰዱ ቻሉ?

በተከሳሽ ጠበቆች አቤቱታ የልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተከሳሾች በመረጡት የጤና ተቋም እና ሆስፒታል ይታከሙ ሲል ፈቅዶ ነበር።

ይሁን እንጂ ከአንድ ሳምንት በፊት የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግን ይግባኝ ተከትሎ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የላንድማርክ ሆስፒታል ሃኪሞች በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ተገኝተው ለተከሳሾች ሕክምና እንዲሰጥ በይኖ ነበር።

ጠበቆች በበኩላቸው የሆስፒታሉ ሠራተኞች በቃሊቲ ማረሚያ የህክምና አገልግሎት ይስጡ መባሉ አግባብ አይደለም በሚል ተከራክረው ነበር። ጠበቆች ደንበኞቻቸው የ24 የህክምና ክትትል አልያም የሕክምና ማሽን ድጋፍ ቢያስፈልጋቸው፤ አገልግሎቱን በማረሚያ ቤቱ ማግኘት አይችሉም በማለት ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ይግባኝ ብለዋል።

ሰበር ሰሚ ችሎቱም ትናንት በዋለው ችሎት ተከሳሾች በሆስፒታሉ ተገኝተው የሕክምና አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችሉ በይኗል።

ሰበር ሰሚ ችሎቱ ይህን ብይን ትናንት ከሰዓት የሰጠው፤ ትናንት ረፋድ ላይ ተከሳሾች በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የነበራቸው ችሎት ተለዋጭ ቀጠሮ ከተሰጠበት በኋላ ነው።

ትናንት ረፋድ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ የክስ መዝገብ የተከሰሱ የ24 ሰዎችን የእምነት ክህደት ቃል ለመቀበል ቀጠሮ ይዞ ነበር። ከእነዚህ መካከል እነ አቶ ጃዋር መሐመድ እና በቀለ ገርባን ጨምሮ 21 ሰዎች በፍርድ ቤት ተገኝተው ነበር።

ይኹን እንጂ ጠበቆች ደንበኞቻቸው እነ አቶ ጃዋር መሐመድ፣ በቀለ ገርባ፣ ሐምዛ አዳነ እና ደጀኔ ጣፋ የረሃብ አድማ ላይ መሆናቸው ለፍርድ ቤት ተናግረው፤ ደንበኞቻቸው አሁን ባሉበት ሁኔታ የእምነት ክህደት ቃላቸውን መስጠት አይችሉም በማለት ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

ዐቃቤ ሕግም ተለዋጭ ቀጠሮ ቢሰጥ እንደማይቃወም ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል።

በዚህም ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የፀረ ሽብርና ሕገ-መንግሥታዊ ጉዳዮች አንደኛ ችሎት የተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃል ለመቀበል ለመጋቢት 6/2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በዚህ ችሎት ላይ የተገኘው የቢቢሲ ሪፖርተር፤ ተከሳሾች አካላቸው ደክሞ እና ከስተው ተመልክቷል። አንዳንድ ተከሳሾች በሰዎች ድጋፍ ወደ ችሎቱ ሲገቡ እና የተከሳሽ ቤተሰብ አባላት መካከል አንዳንዶቹ በችሎት ውስጥ ሲያለቅሱ ሪፖርተራችን ተመልክቷል።

እነ አቶ ጃዋር መሐመድ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ጋር በተያያዘ ከተፈጠረው ሁከት ጋር ተያይዞ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ይታወሳል።

እነ አቶ ጃዋር ከቀረቡባቸው ተደራራቢ አስር ክሶች ስድስቱ እንዲቋረጡ ፍርድ መወሰኑ ይታወሳል።