ኮሮናቫይረስ፡ ቻይና ለኮቪድ-19 ምርመራ ከአሜሪካ ዲፕሎማቶ ላይ ተወሰደ በተባለ ናሙና ተወዛገቡ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ቻይና ከአሜሪካ ዲፕሎማቶች ፊንጢጣ ላይ ለኮሮናቫይረስ ምርመራ በሚል ናሙና እንዲወሰድ አላደረኩም ስትል ተናገረች።
የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ዲፕሎማቶች በዚህ መንገድ ናሙና እንዲሰጡ መደረጋቸውን በመግለጽ ቅሬታ ማሰማታቸውን ዘግበው ነበር።
የተወሰኑ የቻይና ከተሞች ባለሙያዎች "በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን በተሻለ መለየት ያስችላል" በማለታቸው የተነሳ ከፊንጢጣ ናሙና ይወስዳሉ።
ቻይና የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በስፋት መቆጣጣር ከቻሉ ውሱን የዓለም አገራት መካከል አንዷ ነች።
የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዣሆ ሊዢን ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የቀረበውን መረጃ መሰረተ ቢስ ነው ሲሉ አጣጥለውታል።
"ቻይና በአገሯ ተቀማጭነታቸውን ያደረጉ ዲፕሎማቶችን ከፊንጢጣቸው ናሙና እንዲሰጡ በጭራሽ አላደረገችም" ብለዋል።
ባለፈው ሳምንት ዋሺንግተን ፖስት የተወሰኑ ሠራተኞች ለአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት እንዲህ ዓይነት ምርመራ እንዲያደርጉ መገደዳቸውን መግለጻቸውን ዘግቧል።
ናሙናው የሚወሰደው ከ3-5 ሴንቲሜትር ርዝመት ያለው መሳሪያ በጥንቃቄ በማሽከርከር ነው።
እንዲህ ዓይነት ምርመራ ምን ያህል ዲፕሎማቶች እንዳደረጉ የታወቀ ነገር የለም።
ረቡዕ ዕለት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት "የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲህ ዓይነት ምርመራ እንዲያደርጉ አልተስማማም፤ ጉዳዩ መፈፀሙን እንዳወቅን ተቃውሟችንንም [ለቻይና] የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አቅርበናል" ብሏል።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምርመራው "በስህተት" መከናወኑን እንደተገለፀለት አክሎ አስረድቷል።
ቻይና ይህንን የምርመራ ዓይነት ያስተዋወቀችው በታኅሣስ ወር ሲሆን ከተለመደው በአፍንጫና ከአፍ ከሚወሰድ ናሙና በተለየ ቫይረሱን ለመለየት ያስችላል ሲሉ ባለሙያዎች ተናግረዋል።
ነገር ግን ይህ ምርመራ የሚያስፈልገው ለተወሰኑ ሰዎች መሆኑን ባለሙያዎቹ ገልፀው በለይቶ ማቆያ ላሉ ሰዎች ብቻ ነው ሲሉ ምክራቸውን ለግሰው ነበር።












