አሜሪካ የኻሾግጂን ግድያ በተመለከተ ምስጢራዊ መረጃ ልትለቅ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ዩናይትድ ስቴትስ የጃማል ኻሾግጂን ግድያ በተመለከተ ከደህንነት መረብ የተገኘ ምስጢራዊ መረጃ ልትለቅ ነው።
መረጃው በፈረንጆቹ 2018 ጃማል ኻሾግጂ ሲገደል የሳዑዲው ልዑል አልጋ ወራሽ እጅ አለበት ወይ የሚለውን የሚዳስስ ነው ተብሏል።
ዋይት ኃውስ እንዳለው መረጃውን ያነበቡት ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ከሳዑዲው ንጉሥ ጋር በቅርቡ ያወራሉ።
ፕሬዝደንት ባይደን አሜሪካ ከሳዑዲ ጋር ያላትን ግንኙነት እንደ አዲስ ሊፈትሹ አስበዋል።
ጃማል ኻሾግጂ ኢስታንቡል በሚገኘው የሳዑዲ ኤምባሲ ውስጥ ጭካኔ በተሞላበት መንገድ ነው የተገደለው።
ልዑል አልጋ ወራሹ መንግሥታቸው በግድያው ላይ እጁ እንደሌለበት በተደጋጋሚ መናገራቸው ይታወሳል።
የሳዑዲ ባለሥልጣናት እንደሚሉት ኻሾግጂን በሕይወት ይዘው እንዲመለሱ የተላኩ ሰዎች ናቸው በጭካኔ የገደሉት።
የሳዑዲ ፍርድ ቤት በጀማል ግድያ እጃቸው አለበት ያላቸውን አምስት ሰዎች በሞት እንዲቀጡ መወሰኑ ይታወሳል።
ነገር ግን ፍርዳቸው ተሻሽሎ በ20 ዓመት እሥራት እንዲቀጡ ባለፈው መስከረም ተወስኗል።
ስለ አዲሱ መረጃ ምን እናውቃለን?
ሐሙስ አመሻሹን ይለቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው መረጃ ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሳልማን ግድያውን አፅድቀዋል፤ 'የቀጥታ ትዕዛዝ ሳይሰጡም አልቀረም' የሚል እንደሆነ አራት የአሜሪካ ባለሥልጣናት ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
ባለሥልጣናቱ እንደሚሉት የአሜሪካ ማዕከላዊ የደህንነት ኤጀንሲ [ሲአይኤ] ነው መረጃውን ያወጣው።
የሳዑዲ ዋና አቃቤ ሕግና ልዑል ሞሐመድ ስለ ግድያው ምንም መረጃ እንደሌላቸው ቢናገሩም በፈረንጆቹ 2019 ግድያው ለሳዑዲ መንግሥት በሚሠሩ ሰዎች ስለተፈፀመ 'ሙሉ ኃላፊነት እንወስዳለን' ብለው ነበር።
ኤንቢሲ የተሰኘው ጣቢያ እንደዘገበው መረጃው በ2018 ወጥቶ የነበረና በሲአይኤ የተገኘ ነው። ነገር ግን በወቅቱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ መረጃውን አስተባብለውት ነበር።
ጋዜጠኛው ጀማል ኻሾግጂ ለአሜሪካው ዋሺንግተን ፖስት ጋዜጣ ይፅፍ ነበር።
ዋሺንግተን ፖስት ከፊሉ መረጃ የተገኘው የልዑል አልጋ ወራሹ ወንድም የሆኑት ልዑል ኻሊድ ቢን ሳልማን በአሜሪካ የሳዑዲ አምባሳደር በነበሩ ወቅት ካደረጉት የስልክ ልውውጥ ነው ብሎ ዘግቦ ነበር።
ልዑል ኻሊድ አሁን የመከላከያ ምክትል ሚኒስትር ናቸው።
ልዑል ኻሊድ ከወንድማቸው በደረሳቸው ትዕዛዝ መሠረት ለኻሾግጂ ደውለው ኢስታንቡል ወደ ሚገኘው ቆንስላ ቢሄድ ምንም እንደማይገጥመው ነግረውት ነበር።
ልዑል ኻሊድ ግን ከጋዜጠኛ ኻሾግጂ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት አልነበረኝ ሲሉ ያስተባብላሉ።
በ2019 የተባበሩት መንግሥታት ልዩ መልዕክተኛ አግነስ ካላማርድ ሳዑዲ 'ሆን ተብሎ ዝግጅት የተደረገበት ግድያ' ኻሾግጂ ላይ ፈፅማለች፤ የነበረው የፍርድ ሂደትም 'የፍትህ ተቃራኒ ነው' ብለው ነበር።
መረጃው አሁን እንዲወጣ ለምን ተፈለገ?
አዲሱ መረጃ እንዲወጣ የተሻተው ጆ ባይደን ከሳዑዲ መንግሥት ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንደ አዲስ ሊያጤኑት ስላሰቡና ከትራምፕ በተቃራኒ ጠንከር ያለ አቋም ለመያዝ ስላቀዱ ነው ተብሏል።
የትራምፕ አስተዳደር መረጃው እንዲወጣ የመጣውን ትዕዛዝ ባለመቀበል ይልቁንስ ከሳዑዲ ጋር የተሻለ ግንኙነት መፍጠር ይሻላል ወደሚል አቅጣጫ ሄዶ ነበር።
የዋይት ኃውስ ቃል አቀባይ ጄን ሳኪ ረቡዕ ዕለት ባይደን ከ85 ዓመቱ ንጉሥ ሠልማን ጋር እንጂ ቀጥታ ከአልጋ ወራሹ ልዑል ጋር እንደማይነጋገሩ አስታውቀዋል።
ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሳልማን የሳዑዲ አረቢያ ንጉሥ ሆነው ባይሾሙም የባሕረ ሰላጤዋን ሃገር እያስተዳደሩ ይገኛሉ።
ጃማል ኻሾግጂ እንዴት ነበር የተገደለው?
የ59 ዓመቱ ጋዜጠኛ ለመጨረሻ ጊዜ የታየው ቱክር፤ ኢስታንቡል ወደሚገኘው የሳዑዲ ቆንስላ ቅጥር ግቢ ሲገባ ነው።
ኻሾግጂ ወደ ቆንስላ በፈረንጆቹ ጥቅምት 2/2018 ያመራው ቱርካዊቷን ዕጮኛውን ለማግባት የሚያስችሉ ወረቀቶች ለመቀበል ነበር።
እንደ ሳዑዲ አቃቤ ሕግ 'ከሆነ ካሾግጂ በግዳጅ ከግቢው እንዳይወጣ ተደርጓል፤ መጠኑ ከፍ ያለ መድኃኒትም ተሰጥቶታል። ለሞቱ ምክንያት የሆነውም ይህ ነው። ከዚያም ሬሳው ተቆራርጦ ከቆንስላው ውጭ ላለ 'ተባባሪ' ተሰጥቶ ነበር። ቅሪቱ እስከዛሬ አልተገኘም።'
ኻሾግጂ በአንድ ወቅት የሳዑዲ መንግሥት አማካሪና የንጉሣዊው ቤተሰብ ቅርብ ሰው ነበር።
ነገር ግን ከሳዑዲ አገዛዝ ጋር ባለመጣጣሙ ምክንያት በፈረንጆቹ 2017 ሃገሩን ጥሎ ወደ አሜሪካ ተሰደደ።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በዋሺንግተን ፖስት ጋዜጣ ላይ የሚወጣ የሳዑዲው ልዑል ሞሐመድን ፖሊሲዎች የሚተች ወርሃዊ ዓምድ ያሳትም ነበር።
ኻሾግጂ ለመጀመሪያ ጊዜ ጋዜጣው ላይ ባሳተመው ፅሑፍ የሳዑዲ መንግሥት ሊያስረኝ ይችላል የሚል ፍራቻ እንዳለው ፅፎ ነበር።
በመጨረሻው ፅሑፉ ደግሞ የሳዑዲን መንግሥት በየመን ግጭት ጣልቃ በመግባቱ ተችቶት ነበር።












