ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጉግል በጋዜጣ ለሚታተሙ ዜናዎች 'ሞቅ ያለ' ክፍያ ሊፈጽም ነው
ጉግል በቢሊየነሩ ሩፐርት መርዶክ ኮርፖሬሽን ለሚተዳደሩ ሚዲያዎች ለሚታተሙ የዜና ይዘቶች ክፍያ ለመፈጸም ተስማማ፡፡
ይህ አዲስ ስምምነት የቢሊየነሩ ሩፐርት መርዶክ ዜና አውታሮች በጉግል ለሚነበብ ማንኛቸውም ዜናዎች ክፍያ እንዲያገኙ ስምምነት አድርገዋል፡፡
ሩፐርት መርዶክ ቢሊየነርና የበርካታ ሚዲያዎች ባለቤት ናቸው፡፡
የዜና አውታሮቻቸው በድረ ገጽ በሚነበቡበት ወቅት ጉግልም ሆኑ ሌሎች የበይነ መረብ መድረኮች ክፍያ እንዲሰጧቸው ከፍተኛ ውትወታ ሲደርጉ ኖረዋል፡፡
በተለይ በአውስትራሊያ የሚገኙ የዜና አውታሮች ይህንን የክፍያ ጥያቄ በአያሌው ገፍተውበት ባለፈው ዓመት ድል ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
ጉግል በአውስትራሊያ ለሚገኙ የተመረጡ ሚዲያዎች ከወዲሁ ለይዘታቸው ክፍያን መፈጸም ጀምሯል፡፡
የኒውስ ኮርፖሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ሮበርት ቶምሰን "ይህ ለ10 ዓመታት ስንታገልለት የነበረ ነገር ነው፡፡ ለኛ ሚዲያ ኩባንያ (ኒውስ ኮርፖሬሽን) ብቻም ሳይሆን ለሌሎች ጋዜጦችም ይህ ትልቅ ድል ነው" ብለዋል፡፡
በቢሊየነሩ ሩፐርት መርዶክ የተያዘው የኒውስ ኮርፖሬሽን ኩባንያ፣ ዘ ሰን (The Sun)፣ ዘ ታይምስ (The Time)፣ ዎልስትሪት ጆርናል (Wall Street Journal)፣ እና አውስትራሊያን (Australian) የተሰኙ ጋዜጦችን በባለቤትነት የያዘ ነው፡፡
ጉግል ባለፈው ዓመት ‹በይዘታቸው ከፍ ያሉ› ዜናዎችን የሚያትሙ ጋዜጦችን ክፍያ ለመፈጸም ቃል ገብቶ ነበር፡፡ ለዚህም የሚውል አንድ ቢሊዮን ዶላር መድቦ ነበር፡፡
በዚህ ዕድል ለመጠቀም በጀርመን፣ በብራዚል፣ በታላቋ ብሪታኒያ በርካታ ጋዜጦችን መዝግቦ መደራደር ጀምሮም ነበር፡፡
ይህ የቢሊየነሩ ሩፐርት መርዶክ የዜና ኮርፖሬሽን (ኒውስ ኮርፖሬሽን) ከጉግል ጋር ያደረገው ስምምነት አውስትራሊያ ዛሬ አዲስ ሕግ ከማውጣቷ ጋር ተገጣጥሟል፡፡
አዲሱ ሕግ ጉግልና ዜና አውታሮች ባይስማሙ ሊያደራድራቸው የሚችል አካል እንዲሰየም የሚፈቅድ ነው፡፡
ጉግል ከአውስትራሊያ መንግሥት ጋር የገባበት አጣብቂኝ እያጨቃጨቀው ነው፡፡ የጉግል ማሰሻ ነገሮች የማይሻሻሉ ከሆነ አገልግሎቴን ላቋርጥ እችላለሁ ሲልም ማስፈራራት ይዟል፡፡
የአውስትራሊያ መንግሥት ከፌስቡክ ጋር በገጠመው አተካራ ፌስቡክ አገልግሎቱን በአውስትራሊያ በከፊል ማቆሙ ዛሬ ተዘግቧል፡፡
ጉግል ለዜና አውታሮች ከሚሰጠው ክፍያ በተጨማሪ የዜና ድርጅቶቹ የትኛው ዜና እየተነበበ ነው በየትኛው ይቀየር የሚሉ ምርጫዎችን ራሳቸው እንዲወስኑ አድርጓል፡፡
ጉግል እና የቢሊየነሩ መርዶክ ኒውስ ሚዲያ ባደረጉትና ለ3 ዓመታት በሚጸናው ስምምነት ማስታወቂያዎችን ለመጋራት፣ በዩትዩብ የቪዲዮ ጆርናሊዝም ለመጀመር መግባባት ላይ ደርሰዋል፡፡
የመርዶኩ ኒውስ ኮርፖሬሽን ከዚህ ቀደም ከአፕልና ከፌስቡክ ኩባንያዎች ተመሳሳይ ስምምነት ማድረጉ አይዘነጋም፡፡
ሮይተርስ እንደዘገበው ጉግል ለ121 ለሚሆኑ የፈረንሳይ አሳታሚዎች ብቻ 76 ሚሊዮን ዶላር ከፍያ ፈጽሟል፡፡ ይህም ከቅጂ መብት ጋር በተያያዘ ያነሱትን ጥያቄ እርግፍ አድርገው እንዲተው ለማግባባት የተደረገ ነው።