ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካ ሴኔት ትራምፕን ለመክሰስ አብላጫ ድምጽ ሳያገኝ ቀረ
የአሜሪካ ሴኔት ምክር ቤት ከካፒቶል ሂል አመጽ ጋር በተያያዘ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን ለመክሰስ የሚያስፈልገውን ሁለት ሶስተኛ የአብላጫ ድምጽ ማግኘት ሳይችል ቀረ።
አብዛኛዎቹ ሴናተሮች፤ ሰባት ሪፐብሊካኖችን ጨምሮ ከ57 እስከ 43 ዶናልድ ትራምፕ እንዲከሰሱ ድምጻቸውን የሰጡ ቢሆንም ሂደቱን ለማስቀጠል ከሚያስፈልገው 67 ድምጽ 10 ጎድሏል።
ይህን ተከትሎ ዶናልድ ትራምፕ ባወጡት መግለጫ ''በአሜሪካ ታሪክ ትልቁ መቋጫ የሌለው ፍለጋ ነው'' ብለዋል።
በቀድሞው ፕሬዝዳንት ላይ ለማስጀመር የሚያስፈልገው አብላጫ ድምጽ ተገኝቶ ቢሆን ኖሮ ዶናልድ ትራምፕ ከዚህ በኋላ በድጋሚ ለፕሬዝዳንትነት መወዳደር አይችሉም ነበር።
ምርጫው ከተካሄደ በኋላ በኮንግረስ ከፍተኛ የሪፐብሊካን ኃላፊው ሴናተር ሚች ማኮኔል ''ዶናልድ ትራምፕ በካፒቶል ሂል ለደረስ ጥቃት ተጠያቂ ናቸው'' ካሉ በኋላ ክስተቱን '' አሳፋሪ፣ ክብር ገፋፊ እንዲሁም ኃላፊነትን በአግባቡ አለመወጣት ነው'' ብለዋል።
ከቀናት በፊት የአሜሪካ ሴኔት የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ላይ ክስ መመስረቱ ሕገ መንግሥታዊ ነው በማለት የክስ ሂደቱን ማስቀጠሉ የሚታወስ ሲሆን የትራምፕ ጠበቆች ደግሞ ዶናልድ ትራምፕ ዋይት ሃውስን ከለቀቁ በኋላ መሰል ክስ ሊቀርብባቸው አይችልም ሲሉ ተከራክረዋል።
ዴሞክራቶች ባቀረቡት ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ ትራምፕ ደጋፊዎቻቸው 'እስከመጨረሻው እንዲታገሉ' መልዕክት ሲያስተላልፉ፤ ይህን ተከትሎም በካፒቶል ሂል ላይ ጉዳት ሲደርስ አስመልክተዋል።
ዲሞክራቱ ጄሚ ራስኪን፤ ይህ ተግባር ትራምፕን በወንጀል ማስጠየቅ አለበት ብለው ተከራክረዋል።
"ይህ የአሜሪካ የወደፊት እጣ መሆን የለበትም። በመንግሥታችን ላይ አመጽ የሚቀሰቅስ ፕሬዝደንት ሊኖረን አይገባም" ብለዋል።
የቀድሞ ፕሬዝደንት ትራምፕ ጠበቆች በበኩላቸው፤ ዶናልድ ትራምፕን በዚህ ሂደት ውስጥ ማሳለፍ ሕገ መንግሥታዊ አይደለም በማለት ተከራክረዋል። ዲሞክራቶችም ይህን እያደረጉ ያሉት ፖለቲካዊ ፍላጎታቸውን ለማሳካት ነው ብለዋል።
ሚች ማኮኔል ቀደም ብለው ዶናልድ ትራምፕ መከሰስ የለባቸውም፤ ከፕሬዝዳንትነታቸው ከወረዱ በኋላ መከሰሳቸው ሕገመንግስታዊ አይደለም በማለት ተከራክረው የነበረ ቢሆንም የቀድሞው ፕሬዝዳንት ፍርድ ቤት ሊቀርቡ እንደሚችሉ ግን አስጠንቅቀው ነበር።
''የቀድሞው ፕሬዝዳንት አጥፍተው የማይጠየቁበት ነገር አይኖርም። አገራችን ጥሩ የሆነ የወንጀል መከላከልና ፍትህ ስርአት አላት፤ የቀድሞ ፕሬዝዳንቶችም ቢሆኑ ከዚህ አያመልጡም። ካጠፉ መጠየቅ አለባቸው'' ብለዋል።
አዲሱ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በበኩላቸው '' ምንም እንኳን ክሱን ለማስቀጠል የአብላጫ ድምጽ ባይገኝም፤ የክሱ ዋነኛ ነጥብ ግን አከራካሪ አይደለም'' ብለዋል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ላይ ክስ እንዲመሰረት ድምጻቸውን የሰጡት ሰባቱ ሪፐብሊካኖች ሊሳ ሙርኮውስኪ፣ ሱዛን ኮሊንስ፣ ቤን ሴስ፣ ቢል ካሲሲ፣ ሪቻርድ በር፣ ሚት ሮምኒ እና ፓት ቱሚ ናቸው።
ምንም እንኳን በሂደቱ ላይ የተሳተፉ ሴናተሮች የግል አይን እማኞችን ለመስማት ድምጽ ሰጥተው የነበረ ቢሆንም በድንገተኛ ምክክር ሂደቱ ወቅት ግን መዘግየቶችን ለማስቀረት ሲባል እማኞቹ ቃላቸውን በጽሁፍ እንዲያቀርቡ ተደርጓል።