ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በጋና የጨቅላ ሕጻናት ቀበኞቹ በቁጥጥር ሥር ዋሉ
በጋና በጨቅላ ሕጻናት ስርቆት እና ዝውውር የተጠረጠሩ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ።
እነዚህ በጤና ተቋማት ውስጥ የሕጻናት ስርቆት ሲያከናውኑ የነበሩ ግለሰቦች የተያዙት ለወራት በዘለቀ ምርመራ ነው ተብሏል።
እንደ ጋና ባለስልጣናት ከሆነ፣ በጤና ተቋማት ውስጥ የወለዱ የተወሰኑ እናቶች ልጃቸው መሞቱ እንደተነገራቸው፣ አቅማቸው ደካማ የሆኑት ደግሞ እንዲሸጡ መበረታታቸውን ተገልጿል።
በወንጀሉ የተጠረጠሩት ሁለት ዶክተሮች፣ አራት ነርሶች፣ ሁለት እናቶች፣ ሁለት የማህበረሰብ ባለሙያዎች እንዲሁም አንድ የልምድ አዋላጅ በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ምርመራውን ያደረጉት ባለሙያዎች፣ በምርመራቸው ወቅት ሁለት ልጆች በ5,000 ዶላር፣ እና በ4,800 ዶላር ለእያንደንዳቸው ከፍለው መግዛታቸውም ተገልጿል።
ወንጀለኞቹ ሊያዙ የቻሉት የጋና የሕክምና ምክር ቤት እና የምጣኔ ሃብትና የተደራጁ ወንጀሎች ምርመራ ቢሮ በጋራ ባደረጉት ምርመራ ነው።
ፖሊስ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ምርመራውን የጀመረው ባለፈው ዓመት አንድ የታክሲ አሽከርካሪ በሰጠው ጥቆማ መነሻነት ነው ተብሏል።
ሁለቱ ዶክተሮች ፍርድ ቤት ቀርበው ጉዳያቸው ተጣርቶ የመጨረሻ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ የሙያ ፈቃዳቸው እንዲሰረዝ ተደርጓል።
ከዚህ ቀደም የኬንያ ፖሊስ ቢቢሲ የሕፃናትን ንግድን አስመልክቶ በሠራው ዘጋቢ ምክንያት ሶስት ከፍተኛ የጤና መኮንኖችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉ ይታወሳል።
የቢቢሲ አፍሪካ አይ ዘጋቢ ፊልም ናይሮቢ ውስጥ የሚገኝ የመንግሥት ሆስፒታል ውስጥ ሕፃናት እየተሸጡ መሆኑን አጋልጧል።
በወቅቱ ሕፃናቱ በ400 ዶላር [15 ሺህ ብር] እየተሸጡ ነው ተብሏል።
የፖሊስ ኃላፊ በጉዳዩ እጃቸው አለበት የተባሉ ሆስፒታሎችና የሕፃናት ማሳደጊያዎች ምርመራ እንዲካሄድባቸው አዟል።
የቢቢሲ አፍሪካ አይ ዘገባ እንደሚጠቁመው አብዛኛዎቹ ሕፃናት አቅመ ደካማ ከሆኑና መንገድ ላይ ከሚኖሩ እናቶች ነው የሚገዙት።
አልፎም ከናይሮቢ ወጣ ብለው የሚገኙ ሕገ ወጥ ክሊኒኮች በዚህ ንግድ ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ ዘጋቢ ፊልሙ አጋልጧል።