ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሕፃናት የሚቸበችቡት ኬንያዊያን በቢቢሲ ዘጋቢ ፊልም ምክንያት ታሠሩ
የኬንያ ፖሊስ ቢቢሲ የሕፃናትን ንግድን አስመልክቶ በሠራው ዘጋቢ ምክንያት ሶስት ከፍተኛ የጤና መኮንኖችን በቁጥጥር ሥር አውለዋል።
የቢቢሲ አፍሪካ አይ ዘጋቢ ፊልም ናይሮቢ ውስጥ የሚገኝ የመንግሥት ሆስፒታል ውስጥ ሕፃናት እየተሸጡ መሆኑን ያሳያል።
ሕፃናቱ በ400 ዶላር [15 ሺህ ብር] እየተሸጡ ነው ተብሏል።
የፖሊስ ኃላፊ በጉዳዩ እጃቸው አለበት የተባሉ ሆስፒታሎችና የሕፃናት ማሳደጊያዎች ምርመራ እንዲካሄድባቸው አዟል።
እስካሁን የተደረጉ ምርመራዎች እንዳጋለጡት ከፍተኛ የፖሊስ መኮንኖችም በሕፃናት ህገ ወጥ ንግድ ተሰማርተው ነበር ብለዋል የፖሊስ ኃላፊ ሂላሪ ሙትያምባይ።
ተጠርጣሪዎች ድምፃቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም።
የቢቢሲ አፍሪካ አይ ዘገባ እንደሚጠቁመው አብዛኛዎቹ ሕፃናት አቅመ ደካማ ከሆኑና መንገድ ላይ ከሚኖሩ እናቶች ነው የሚገዙት።
አልፎም ከናይሮቢ ወጣ ብለው የሚገኙ ሕገ ወጥ ክሊኒኮች በዚህ ንግድ ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ ዘጋቢ ፊልሙ አጋልጧል።
ማማ ሉሲ ኪባኪ በተሰኘው የመንግሥት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ሙስና እንዳለ በዘጋቢ ፊልሙ ታይቷል።
በፊልሙ ላይ ፍሬድ ላፓራን የተባለ የሆስፒታል ሠራተኛ ልጅ መግዛት እንፈልጋለን ብለው ለቀረቡት የፊልሙ አዘጋጆች የሁለት ሳምንት አራስ ወንድ በ200 ሺህ ሺልንግ [2700 ዶላር ወይም 103 ሺህ ብር ገደማ] ጥሬ ገንዘብ ሲሸጥ ይታያል።
ፍሬድ ላፓርንም ሆነ ማማ ሉሲ ኪባኪ የመንግሥት ሆስፒታል በጉዳዩ ላይ አስተያየት ተጠይቀው ተባባሪ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
ማክሰኞ ዕለት ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የሠራተኛና ማሕበራዊ ጥበቃ ሚኒስትሩ ሳይመን ቼሉጊ ድርጊቱን የፈፀሙት ሰዎች 'ከባድ ሕጋዊ ቅጣት' ይጠብቃቸዋል ብለዋል።
ሚኒስትሩ አክለው ለሕፃናት የሚደረገው ጥበቃ የበለጠ ሊጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።
የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ሠራተኛው ፍሬድ ማቲያንጊ ቢቢሲን ለዘገባው አመሰግነው ሕገ ወጥ የሰው ልጅና የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ለምስራቅ አፍሪቃዊቷ ሃገር ፈተና እንደሆነ ተናግረዋል።
ምንም እንኳ ምን ያክል ሕፃናት በሕገ ወጥ መንገድ እየተዘዋወሩ እንዳለ ባይታወቅም ሚሲንግ ቻይልድ ኬንያ የተሰኘው መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም ባለፉት ሶስት ዓመት 600 ሕፃናት ሳይሸጡ እንዳልቀረ አሳውቋል።