በካሜሮን ታግተው የነበሩት የቀድሞው ሊቀ ጳጳስ ተለቀቁ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በካሜሮን የግጭት ማዕከል በሆነው አንግሎፎን (እንግሊዘኛ ተናጋሪዎች) አካባቢ ታፍነው ተወሰደው የቆዩት የ90 ዓመቱ የቀድሞ ሊቀ ጳጳስ ነፃ ወጥተው ህክምና እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡
አብረዋቸው የታፈኑት ሌሎች 10 ሰዎች የት እንዳሉ ግን እስካሁን አልታወቀም ተብሏል፡፡
ጡረታ የወጡት የቀድሞው ሊቀ ጳጳስ ክርስቲያን ቱሚ ሐሙስ ዕለት ከዋና ከተማዋ ያውንዴ ወደ ኩምቦ ሲጓዙ ነበር የታገቱት፡፡
የተለቀቁበት ሁኔታም ግልፅ አይደለም፡፡
ለሊቀ ጳጳሱ ቅርብ ናቸው የሚባሉት ኤሊ ስሚዝ ለቢቢሲ እንደገለፁት አጋቾቹን ባነጋገሩበት ወቅት ቄሱን ያገቷቸው ለመንግሥት መልእክት ለማስተላለፍ ብቻ መሆኑን ተጨማሪ መረጃን ሳይገልጹ እንደነገሯቸው አስረድተዋል።
የኩምቦ ጳጳስ ከእገታው በስተጀርባ ያሉት ተገንጣዮች መሆናቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል ፡፡
በተጨማሪም በርካታ የኩምቦ ነዋሪዎች ታጋቾችን በመፈለግ ከእስር እንዲለቀቁ በመጠየቅ ወደ ተገንጣዮች ካምፕ ማምራታቸውን ተናግረዋል ፡፡
የእንግሊዝኛ ተናጋሪ ቡድኖች እ.ኤ.አ. ከ2016 ጀምሮ ለነጻነት የሚያደርጉትን ትግል ተከትሎ የካሜሮን የተወሰነ ክፍል በግጭት እየታመሰ ይገኛል። በአብዛኛው ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ከሆኑት የሀገሪቱ ባለሥልጣናት ይገጥመናል ያሉትን አድልዎ ደግሞ እንደ ምክንያት አቅርበዋል።
በዚያው ሳምንት በኩምቦ በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት 11 መምህራን በተገንጣዮች ታፍነው በኋላ ተለቀቅዋል፡፡
ባለፉት ቀናት በእንግሊዝኛ ተናጋሪ በሆኑት በኩምባ እና ሊምቤ ከተሞች በሚገኙ ሁለት የተለያዩ ትምህርት ቤቶች ላይ የተፈፀሙ ጥቃቶችም ቁጣቀስቅሰዋል፡፡ በቅርቡ በኩምባ ማዘር ፍራንሲስካ ትምህርት ቤት ላይ በደረሰ ጥቃት ሰባት ልጆች ተገድለዋል።
ለአምባዞኒያ መንግሥት ነፃነት በሚታገሉ ተገንጣዮች ዛቻ በካሜሩን አንግሎፎን ክልሎች ውስጥ ያሉ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ለአራት ዓመታት ተዘግተው በቅርቡ ነበር የተከፈቱት፡፡
ስለ አጋቾቹ ሰዎች ምን እናውቃለን?
ከታገቱት መካከል ከኩምቦ ከተማ በቅርብ ርቀት የምትገኘው የንሶ መንደር ባህላዊ ገዥ ይገኙበታል፡፡
ሴህም ምቢንግሎ ሁለት ወንድ ልጆቹ ተገንጣይ ተዋጊዎች እንደሆኑ በሚጠረጠሩ ግለሰቦች ከተገደሉ እና እሳቸውም የሞት ማስፈራሪያ ሲደርስባቸው ከወራት በፊት ንሶን ለቅቀው ሸሽተዋል።
የዚሁ መንደር ተወላጅ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ቱሚ በባህላዊው ገዥ እንዲመለሱ በቅርቡ ድርድር አካሂደዋል፡፡ ድርድሩን አካሂደው ሲመለሱ ነው እሳቸው እና ሌሎች ዘጠኝ ሰዎች የታገቱት።
በቅርቡ በጡረታ ከሥራቸው የተገለሉት ቄሱ መንግሥትን በመተቸት የሚታወቁ ሲሆን የአንግሊዝኛ ተናጋሪ አካባቢን ቀውስ ለመፍታት ፌዴራሊዝም ሥርዓት ወሳኝ ነው ሲሉ ይደግፋሉ።
መንግስት ችግር ለገጠመው የሰሜን-ምዕራብ ክልል "የሰላም ተጓዥ" ቡድንን እንዲመሩ ሲመርጣቸው የማስታረቁንም ሚና ተጫውተዋል፡፡
ግጭቱ ምንድነው?
በካሜሩን የእንግሊዝኛ ተናጋሪዎች በሚበዙባቸው በሰሜን-ምዕራብ እና በደቡብ-ምዕራብ አካባቢዎች ፈረንሳይኛ እና በትምህርት ቤቶች እና ፍርድ ቤቶች የመጠቀሙ አዝማሚያ መጨመሩን የሚቃወሙ ሰልፎች እ.ኤ.አ. በ2017 ወደ አመፅ ተቀይረዋል።
የፀጥታ ኃይሎች እርምጃ መውሰዳቸው አንዳንድ እንግሊዝኛ ተናጋሪ ሲቪሎች ፈረንሳይኛ ተናጋሪ በሆኑት በፕሬዝዳንት ፖል ቢያ በሚመራው በመንግስት ላይ መሳሪያ እንዲነሱ አድርጓቸዋል፡፡
የተገንጣዮች እና የፀጥታ ኃይሎችን ግጭት ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ተፈናቅለዋል።












